ዜና ዜና

ኢትዮጵያ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በኤሌትሪክ ኃይልና በማዕድን ዘርፎች ከካናዳ ጋር በጋራ መስራት እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ ።

የአፈር፣ የውሃና የአየር ብክለትን በመቀነስ ጤናማ ምርት የሚመረትበትን አግባብ ለማጠናከር የተፈጥሮ ግብርና ፖሊሲ እንዲቀረጽለት ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት አስታወቀ፡፡

ማዕከሉ ‹‹በተፈጥሮ ግብርና የተመረተ ምግብ ለሁሉም›› በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት በአዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች መሰብሰቢያ አዳራሽ የአረንጓዴ ንቅናቄ ሳምንት ውይይት በተካሄደበት ወቅት የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛው ገብረማርያም እንደተናገሩት የአፈር፣ የውሃና የአየር ብክለትን በመቀነስ ጤናማ ምርት የሚመረትበትን አግባብ ለማሳደግና ዘላቂ የሆነ ግብርና ለመፍጠር ማዕከሉ ራሱን የቻለ የተፈጥሮ ግብርና ፖሊሲ እንዲቀረጽ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡

ማዕከሉ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ብዝሃ ሕይወት የሚያገግምበትን አቅጣጫ ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ጤናማ የግብርና ምርቶች ተመርተው ለዜጋው የሚቀርቡበትን አማራጭ ከማስፋት አኳያ ከመንግሥት የፖሊስ አቅጣጫ ጋር በመደጋገፍ ግብርናው ዘላቂ ሊሆን የሚችልበትን አግባብ እየፈጠረ እንደሚገኝ አቶ ግዛው ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ግዛው ገለጻ፤ ማዕከሉ አሳታፊ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በገጠርና በከተማ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ለአርሶ አደሩ ዘመን ተሻጋሪ የግብርና ዘዴ በመጠቀም ምርታማነትን እንዲያሳድግና ጤናማ ምርቶችን እንዲያመርት ለማድረግ ድጋፎችን እያደረገ ነው፡፡ በተፈጥሮ ግብርና ለሚመረቱ ምርቶች የገበያ ትስስር በመፍጠር አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን፤ የተፈጥሮ ግብርናን ማዕከል ያደረገ የፖሊሲ ቅኝት እንዲኖር እየሰራ ነው፡፡

በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት ከፍተኛ የማህበረሰብ አስተባባሪ ወይዘሮ አዜብ ወርቁ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ግብርናን ማዕከል ባደረገ መልኩ ምርቶችን እንዲያመርት ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑንና እስካሁንም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በማዕዛማ ተክሎችና ልዩ ልዩ ሰብሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ ለረዥም ጊዜ በትግራይ ክልል በመስራት እመርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ የቻለ መሆኑንና በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ሆለታ፣ ወሊሶ፣ በአማራ ደቡብ ወሎ፣ ሐይቅ፣ በደቡብ ከምባታንና ጠምባሮ ዞን ቀጨቢራ ወረዳ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ለተፈጥሮ ግብርና አምራቾች ከለላ የሚሰጥና የሚያረጋግጥ አካል ስለሚያስፈልግ ራሱን የቻለ ፖሊሲ እንዲቀረጽለት ጥረት እየተደረገ መሆኑን፤ ይህም ሸማቹ በሚገዛው ምርት እምነትና ዋስትና እንዲያድርበት እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ አዜብ ገለጻ፤ ከአመራረት አኳያ በአዋጁ እውቅና ያላቸው ደረጃዎችን ለአብነት የምሥራቅ አፍሪካ የተፈጥሮ ግብርና ደረጃ፣ የዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ግብርና ፌዴሬሽን ደረጃ መጠቀም እንደሚቻል ቢገለጽም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በኢትዮጵያ የአፈጻጸም መመሪያና ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፣ ጥቅምት 24/2010