ዜና ዜና

አርሶ አደሩ የደረሰ ሰብልን በወቅቱ ሊሰበስብ ይገባል- የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ

በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ የደረሰ ሰብልን ያለመዘናጋት ሊሰበስብ እንደሚገባ የክልሉ ግብርና ቢሮ አሳሰበ።

የቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ቁምላቸው እንደገለጹት ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለይ በምዕራብ አማራ አካባቢ በአሁኑ ወቅት ያለማቋረጥ እየጣለ ነው፡፡

የሚጥለው ዝናብ በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶአደሩ አደረጃጀትንና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰበስብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሚሰበሰበውን ሰብልም ከእርጥበት ነፃ አድርጎ በማናፈስ፣ በማዳረቅና ከመሬት ከፍ አድርጎ በመከመር የምርት ጥራቱ እንዳይጓደል መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በየቀበሌው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም በአሁኑ ወቅት ለአርሶአደሩ ስለሰብል አሰባሰብና መሰል ስራዎች በቅርበት ሆነው ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

እስካሁን ከ527 ሺህ 250 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ተዘርቶ የደረሱ የገብስ፣ የሰሊጥ፣ ጤፍ፣ ቦሎቄ፣ አተርና ባቄላ ሰብል ተሰብስቧል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ እየጣለ ያለውን ዝናብ አርሶአደሩ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ፈጥነው የሚደርሱ የጥራጥሬ ሰብሎችን ማልማት  እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ ትንተና፣ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ንጋቱ መልሴ በበኩላቸው ''ዝናቡ እስከተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚቀጥል የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች  ይጠቁማሉ'' ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በምዕራብ አማራ አካባቢ እየጣለ ያለው ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶአደሩ የደረሰ ሰብል መሰብሰብ እንዳለበት መክረዋል።

"የቤተሰባቸውን ጉልበት በማስተባበር የደረሰ ሰብልን እየሰበሰቡ መሆናቸውን" የተናገሩት ደግሞ በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የይጎዲ ቀበሌ አርሶ አደር ጥበቡ አበራ ናቸው።

ያላቸውን ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት በበቆሎ፣ ዳጉሳ፣ ገብስ፣ ጤፍና በርበሬ ሰብል ያለሙ ሲሆን እስካሁንም የደረሰ የገብስና የበርበሬ ሰብል መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።

በዚሁ ወረዳ የጨንታ ሶስቱ ቀበሌ አርሶ አደር ፈንታ አብተው በበኩላቸው ዝናቡ ያለማቋረጥ እየጣለ በመሆኑ የደረሰ ሰብል ለመሰብሰብ እንዳስቸገራቸው ተናግረዋል።

ቢሆንም ግን አደረጃጀታቸውን በመጠቀም የበቆሎና የጤፍ ሰብልን እያጨዱ በባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ መሠረት በማዳረቅና በማናፈስ እየሰበሰቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በዘንድሮው የመኽር ወቅት በክልሉ በተለያዩ ሰብሎች ከለማው ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ከ130 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  

 ባህር ዳር ጥቅምት 14/2010(ኢዜአ)