ዜና ዜና

የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች የልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ ተገለጸ

የፌዴራል መንግስት የዓመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች የሀገሪቱን ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታን ሊያጠናክሩ እንደሚችሉ በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለሁለቱ ምክር ምክር ቤቶች የጋራ መደበኛ ስብሰባ ላይ የዓመቱን የመንግስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክተው ንግግር ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡

ይህንን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ፣ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መንግስት የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ ነው፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አሻግሬ ስዩም በሰጡት አስተያየት በፕሬዝደንቱ የተመለከቱት የዓመቱ የመንግስት ትኩረት አቅጣጫዎች መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ከህዝብ ጋር በመወያየት የለያቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮችና የመንግስት ሰራተኞች ግንዛቤ መፍጠሩ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው "ይህንን ስራ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማከናወን መታቀዱም መልካም ነው "ብለዋል፡፡

መንግስት ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎችንና ባለሙያዎችን ተጠያቂ ማድረግ መጀመሩንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር ጠቅሰዋል፡፡

ይህም መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን ለመታገል የደረሰበትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ነው አስተያየት ሰጪው የተናገሩት፡፡

በፕሬዝዳንቱ ንግግር የመምህራን ጉዳይ መካተቱ መንግስት ለመምህራን ልማት የሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይ የገለፁት ደግሞ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ዳምጠው ተሰማ ናቸው፡፡

የመምህራንን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻልና የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ከማድረግ አኳያ አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በክልሎች የሚገኙ ናቸው፡፡

የክልል መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

"በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህራን ቅጥር በአካባባዊነት የሚፈፀም መሆኑ ለትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት ሊሆን ስለሚችል የተጠናከረ ክትትል ማድረግ ይገባል" ብለዋል፡፡
ኢዜአ፣ አሶሳ ጥቅምት 1/2010