ዜና ዜና

የኢትዮ-ቦትስዋና የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በጋቦሮኒ ተካሄደ

የኢትዮ- ቦትስዋና የመጀመሪያው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ትናንት  በቦትስዋና ጋቦሮኒ መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ስብሰባው የሁለቱን አገሮች ታሪካዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገርና ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የጋራ ኮሚሽን ስብሰባው በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ እና በቦትስዋና የአለም አቀፍ ጉዳዮችና ትብብር ሚኒስትር ዶ/ር ፔሎኖሚ ቬንሰን ሞይቶይ ንግግር ነው በይፋ የተጀመረው፡፡

ሚኒስትሮቹ ሀገሮቹን የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ እና ታሪካዊ ግንኙነቱን የበለጠ ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በኢፌዲሪ የእንስሳት እና አሳ ሃብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ እና በቦትስዋና የግብርና ልማት ሚኒስትር መካከል በእንስሳት እና በአሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ትብብር ላይ የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውም እንዲሁ፡፡

በስብሰባው የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወልደማርያም ተገኝተዋል፡፡

የሁለቱ ሃገራት ሁለተኛው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

ጥቅምት 1/2010 /ኢዜአ/