ዜና ዜና

ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ስኬት ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ ማጠናከር አለበት---የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስታወቁ።

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገረቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጋምቤላ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ችቦ የአቀባበል ስነ- ስርዓት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።

በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ ምክትል አፈ-ጉባኤው አቶ ጁል ናንጋል እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነትና የኩራት መገለጫ ለሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የክልሉ ሕዝብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

''ያለማንም ድጋፍና እርዳታ የኢትዮጵያ ህዝብ  ባለው  ሀብት፣ እውቀትና ጉልበት የጀመረው ግድብ  እውን እስኪሆን ዛሬም እንደ ትናንቱ ድጋፋችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል'' ብለዋል።

ግድቡ በተለይም ለተጀመረው  የልማት፣ የፀረ- ድህነት ትግልና የህዳሴ ጉዞ ስኬት የላቀ ጠቀሜታ የሚኖረው በመሆኑ ህዝቡ ድጋፉን በቦንድ ግዥም ሆነ በስጦታ ሊያጠናክር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ኡኳይ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የክልሉ ህዝብ ከእዚህ ቀደም ለግድቡ ግንባታ በቦንድ፣ በሎተሪ ግዥና በስጦታ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

ግድቡ በህዝብ ተሳትፎ የሚገነባ እንደመሆኑ በቀጣይም የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተጀመረው ገቢ የማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የህዳሴውን ግድብ ችቦ በክልሉ ሦስት የብሔረሰብ ዞኖች በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች በማዘዋወርና ህዝቡን በማነሳሳት በተያዘው በጀት ዓመት 60 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አንዳንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ እውን እስኪሆን ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የጋምቤላ ክልል የንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዝዳንት አቶ ቸኮል በለጠ ግድቡ ከድህነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ከእዚህ ቀደም በሁለት ዙር የ75 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ በመፈጸም ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ቸኮል፣ በቀጣይም ተጨማሪ የቦንድ ግዥ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን በቦንድ ግዥም ሆነ ሌላ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ እንደሆኑ የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ቴዎድሮስ መኮንን ናቸው።

ግድቡ የሀገሪቱን እያደገች መምጣት ከሚያረጋግጡ ማሳያዎች አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዛሬው ዕለት ችቦው በጋምቤላ ስታዲየም አጀብ ተደርጎለት ለከተማ መስተዳድሩ የቅብብሎች ስነ ስርዓት ተካሄዶለታል።

ጋምቤላ ጥቅምት 1/2010 /ኢዜአ/