ዜና ዜና

በአፋር የመሰረተ-ልማት ስራዎች እንዲጠናከሩ ድጋፍ አደርጋለሁ- የትራንስፖርት ሚኒስቴር

በአፋር ክልል እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን የሚያስተናግደው አፋር ክልል ሰመራ እየተከናወኑ ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያና ሌሎችንም የመሰረተ ልማት ስራዎች የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ተመልክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት  በአፋር እየተከናወኑ ያሉት የመሰረተ ልማት ስራዎች ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው፡፡

በተለይም ከአጭር ግዜ አንጻር በቅርቡ ከሚከበረው 12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጋር ተያየዞ የሚከነወኑ የመሰረተ-ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ መንግሰት ጋር በመተባባር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ቀደም ብሎ የተጀመሩ የሰመራ አውሮፕላን ማረፊየና የመንገድ ግንባታዎች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ መሰረት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ የሚከናወኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ሰራዎች የሃገሪቱን ወጪና ገቢ ንግድ በማቀላጠፍ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የበለጠ እንዲጠናከሩ  ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጰያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አርአያ ግርማ በበኩላቸው አፋር ከሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር የሚያገናኙ ልዩ ልዩ የመንገድ ስራዎች  በእቅዳቸው መሰረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ያለውን  እምቅ የተፈጥሮ ሃብትና የቱሪስት መስህብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚስችሉ የዲዲግሳአላ-ያሎ-ኒኤሌ መንገድና የአዋሽ አርባ-ዱለሳ-ደብረብርሃን እንዲሁም የዳሉል-ባዳ መንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም  በጀት ዓመቱ ወደስራ የሚገቡ ከአህመዴአ- አፍዴራና ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ከ12ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ጋር ተያየዞ   የ3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሰመራ ከተማ የአስፓልት መንገድ ማስፋፋያ ስራ እየተከናወነ መሆኑንና ለበዓሉ እንደሚደርስም ጠቅሰዋል፡፡

የአፍሮጺዮን ኮንስትራክሽን ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ላይችሉህ መጨጌያው እንዳሉት 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ ወደ አስፓልት ደረጃ የማሳደግ ስራው 94 በመቶ ተጠናቋል፡፡

የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ግንባታ በማጠናቀቅ ለበዓሉ እንግዶችን ማስተናገድ በሚችልበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ድርጅታቸው ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ሰመራ ጥቅምት 01/2010 /ኢዜአ/