ዜና ዜና

በሐረሪ ክልል እያደገ የመጣውን የጎብኚዎች ቁጥርና የዘርፉን ገቢ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው

የሐረሪ ክልል ቱሪዝም ምክር ቤት በክልሉ እያደገ የመጣውን የጎብኚዎች ቁጥርና ከዘረፉ የሚገኘውን ገቢ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰራ ነው።

አለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን በክልል ደረጃ ትናንት በሐረር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ያስሚን ዘካርያ እንደገለፁት በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ የመስህብ ስፍራዎችን የሚጎበኙ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜጎች ቁጥር በየዓመቱ እድገት እያሳየ ነው።

"በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት በክልሉ የሚገኙ የመስህብ ስፈራዎችን ከጎበኙ 107 ሺህ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል" ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በጎብኚዎች ቁጥርም ሆነ በገቢ የተመዘገው ውጤከ2006 ዓመት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ብልጫ እንዳለው ለአብነት ጠቅሰዋል ።

እያደገ የመጣውን የጎብኚዎች ቁጥርና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ አጠናክሮ ለማስቀጠል በዚህ ዓመት ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ የቱሪዝም ምክር ቤት በክልል ደረጃ ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ።

ምክር ቤቱ የቱሪስት መስብ መዳረሻዎችን ለጎብኚዎች መቹ ከማድረግ ጀምሮ በዘርፉ ከአገልግሎት አሰጣት ጋር የሚታዩ ችግሮችና መሰል ተግዳሮቶችን በጥናት ለይቶ ለመፍታት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎብኚዎችን ተቀብለው በሚያሰተናግዱ የሆቴል ተቋማትና አስጎብኚ ማህበራት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል ለሥራ ኃላፊዎቻቸውና ለሰራተኞቻቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ከክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ወደ መስህብ ስፍራዎች የሚያደርሱ መንገዶችን ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ወይዘሮ ያስሚን ጠቅሰዋል።

"የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም በኩል ያሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት በዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት የታገዘ የጥናትና ምርምር ሥራ  እየተካሄደ ነው" ብለዋል።

በፓናል ውይይቱ ላይ ከተሳተፉት መካከል በከተማው በአስጎብኚነት ስራ የተሰማሩት አቶ ቴዎድሮስ በላይ እንዳሉት  

በከተማው የአካባቢ ንጽህና አጠባበቅ ጉድለት ለመፍታትና መንገዶችን ምቹ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አመልክተዋል።

"ቢሮው በከተማው ከሚገኙ ሆቴሎች ጋር በመቀናጀት ለተቋማቱ ሠራተኞች እየሰጠ ያለው ስለጠናና የክትትል ስራ በስራችን ላይ ለውጥ እንድናመጣ አድርጎናል" ያሉት ደግሞ የበላይነህ ሆቴል ተወካይ አቶ ዮናስ ወልደማሪያም ናቸው።

በከተማው በተለያዩ ስፍራዎች የሚታየውንና በጎብኚዎች የሚዘወተረውን "የጅብ ምገባ ትርኢት" በአንድ ቦታ ለማሳየት የተጀመረው የግንባታ ስራ በፍጥነት እንዲጠናቀቅም ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።

በሐረሪ ክልል በቱሪስቶች ከሚጎበኙት ቅርሶች መካከል በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባው ታሪካዊ የጀጎል ግንብና በውስጡ የሚገኙ ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶችና አምስቱ መግቢያ በሮች ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪ ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶች፣ የፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራንቦ መኖሪያ ቤት፣ የሐረሪ ብሔረሰብ ሙዚየሞች፣ አድባራትና የጅብ ምገባ ትርኢት ተጠቃሽ ናቸው።

ሀረር ጥቅምት 1/2010 /ኢዜአ/