ዜና ዜና

ምክር ቤቱ የአማራና ቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው ቀበሌዎች የተደረገውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት አፀደቀ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የአማራና ቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው ስምንት ቀበሌዎች የተደረገውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት በዛሬው እለት አፅድቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው፥ በሰሜን ጎንደር አራት ወረዳዎች በሚገኙ ስምንት ቀበሌዎች በተካሄደው ህዝብ ውሳኔ ሰባቱ በነባሩ አስተዳደር እንዲከለሉ ድምፅ ስጥተዋል።

አንድ ቀበሌ ደግሞ በቅማንት ራስ አስተዳደር ለመተዳደር ነው ድምፅ የሰጠው።

በዚህም መሰረት በጭልጋ ወረዳ የኳበር ሎምዩ የተባለች ቀበሌ በቅማንት አስተዳደር ስር ስትካለል፥ ቀሪዎቹ ሰባት ቀበሌዎች በነባሩ አስተዳደር የሚካለሉ መሆኑን ውጤቱ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ፀሃፊ እና የጽህፈት ቤቱ ዋና ሃላፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝበ ውሳኔ አፈፃፀሙን ሪፖርት አቅርበዋል።

የአማራና የቅማንት ህዝብ ተቀላቅለው በሚኖርባቸው 8 ቀበሌያት 23 ሺህ 283 ነዋሪዎች በመራጭነት መመዝገባቸውን በሪፖርታቸው አብራርተዋል።

ከተመዘገቡት ውስጥ በምርጫ ጣቢያ በመገኝት 20 ሺህ 824 ነዋሪዎች ወይም 89 በመቶ በዕለቱ ፍላጎታቸውን ድምፅ በመስጠት መግለፃቸውን ተናግረዋል።

ሂደቱን ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ እና ገለልተኛ መንገድ ማከናወን መቻሉንም ለምክር ቤቱ በሪፖርታቸው አቅርበዋል።

የአማራ ክልል አስተዳደር በቀሪ አራት ቀበሌዎች ከህዝቡ ጋር የሚያደርገው ውይይት ባለማጠናቀቁ የምርጫ ቦርድ የህዝብ ውሳኔውን ማካሄድ አለመቻሉን አስታውቀዋል።

ይህንንም ህዝበ ውሳኔውን ከማከናወኑ በፊት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳወቀ እና ምክር ቤቱም የክልሉ አስተዳደር ከህዝቡ ጋር የሚያደርገውን ውይይት በመገንዘብ የምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት በስምንቱ ቀበሌያት ላይ ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ አድርጓል።

በቀሪ አራት ቀበሌዎች ላይ የክልሉ አስተዳደር ለፌዴሬሽን ምከር ቤት በሚያቀርበው ጥያቄ ላይ በመመስረት ውሳኔ እንደሚያስልፍ ይጠበቃል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ሪፖርት የህዝበ ውሳኔ ሂደቱ የህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎና ውሳኔ በትክክል ተግባራዊ መድረጉን የሚያሳይ ነው በማለት ውጤቱን አፅጽድቆታል።

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ)