ዜና ዜና

ኢትዮጵያና ኢራን የንግድ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩ አስታወቁ፡፡

የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስትር ዶክተር በቀለ ቡላዶ ከኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል መህዲ አቃ ጃፋሪ ጋር ተገናኝተው የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ማሳደግ ስለሚቻልበት ሁኔታ ተነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት ቀጥታ የንግድ ግንኙነት ማጠናከርን፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ትርኢቶች ማካሔድን ጨምሮ የተግባቦትና የባንክ ትብብርን ማጎልበትና የቢዝነስ ጉብኝቶችን ማመቻቸት የሚቻልባቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ንግድ ሚኒስትር ዶክተር በቀለ ቡላዶ ሀገራቸው ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ እንዲሁም የኢኮኖሚና ንግድ ትብብሩን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል፡፡

የኢራኑ ዲፕሎማት ኡጋንዳንና ቡሩንዲን ጎብኝተው ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝታቸው ማሳረጊያ አድርገዋታል፡፡

በኢትዮጵያ ቆይታቸውም ከኢፌዴሪ ማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትርና ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ ጀነራል ዳይሬክተር ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል ፡፡

በአዲስ አበባ ቆይታቸው የሚገኘውን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ የጎበኙ ሲሆን ከሃላፊዎቹ ጋርም ሀሳብ መለዋወጣቸውን የኢራን ዜና አገልግሎት (IRNA) በድረ ገጹ ማስነበቡን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ኢዜአ፣ ጥቅምት 1/2010