ዜና ዜና

በሀገሪቱ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት ተችሏል

በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት እንደተቻለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሸን ገለጸ።

ኮሚሽኑ እ.አ.አ ከ2010/11 እስከ 2015/16 የነበረውን የኢትዮጵያ የድህነት ምጣኔ የሚያሳይ የዳሰሳ ጥናት ትንተና ውጤት ይፋ አድርጓል።

ጥናቱ በሁሉም የሀገሪቷ ገጠርና ከተማ የሚኖሩ 30 ሺህ 255 የቤተሰብ ኃላፊዎችን በናሙናነት የወሰደ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩ.ኤን.ዲፒ) እና የልማት አጋር ቡድን (ዳግ) በቴክኒክና በግብዓት ድጋፍ ተሳትፈውበታል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም እንደገለጹት፤ በድህነት የሚኖሩ ዜጎችን ምጣኔ በ2010/11 ከነበረበት 29 ነጥብ 6 በመቶ በ2015/16 ወደ 23 ነጥብ 5 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

ምንም እንኳን ጥናቱ በተካሄደባቸው ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ ቁጥር ቢጨምርም በድህነት የሚኖሩ ዜጎች ቁጥር መቀነሱን ነው የተናገሩት።

በተጠቀሱት አምስት ዓመታት የምግብ አቅርቦት ችግር በተመሳሳይ ከ33 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 24 ነጥብ 8 በመቶ ዝቅ ያለ ሲሆን፤ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢም ከ377 ወደ 794 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ብሏል።

ለድህነት ምጣኔው መቀነስ በከተማና በገጠር በመንግሥት የተተገበሩ ድህነት ተኮር የልማት ተግባራት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

መንግሥት በተለይ የገጠሩን ማኅበረሰብ ከድህነት ለማውጣት በርካታ ተግባራትን ቢያከናውንም በአንጻሩ በገጠር አካባቢ ያለው የድህነት ምጣኔ ከከተማው ከፍ እንደሚል ነው የተናገሩት።

አቶ ጌታቸው በተመሳሳይ የአምስት ዓመት ጊዜ የገቢ ልዩነት ምጣኔ መመዘኛ (ጊኒ ኮፊሸንት) ከነበረበት 0 ነጥብ 30 ወደ 0 ነጥብ 33 ማደጉን ገልጸው "ይህ አነስተኛ ጭማሪ በሃብታምና ደሃ መካከል የተጋነነ የገቢ ልዩነት እንደሌለ ያሳያል" ነው ያሉት።

ጥናቱን በቴክኒክና ግብዓት የደገፈውን የልማት አጋር ቡድን የወከሉት አንድሬ ገሂኦኔ ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚዊ ዕድገትና የማኅበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሎችን እንዳስመዘገበች ጠቁመው በጥናቱ ሰፊ ዳሰሳ መደረጉን ገልጸዋል።

"ጥናቱ በቀጣይ የኢትዮጵያ መንግሥትና አጋር ድርጅቶች በሀገሪቱ ድህነትን ለመቀነስ ለሚያከናውኑት ተግባር መሠረታዊ ፋይዳ አለው" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው መንግሥት በኤልኒኖ አማካኝነት የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል 13 ቢሊዮን ብር መድቦ በመሥራቱ ድርቁ በድህነት ምጣኔ ምዘና ላይ የጎላ ልዩነት እንዳላመጣ ተናግረዋል።

መንግሥት የድርቁን አደጋ ለመከላከል የተጠቀሰውን ብር መድቦ ባይንቀሳቀስ ኖሮ የድህነት ምጣኔው 28 በመቶ ይሆን እንደነበርም አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የቤተሰብ ገቢና ፍጆታ ወጪ እንዲሁም የኑሮ ደህንነት ክትትል ጥናት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን እ.አ.አ ከ1995/96 ጀምሮ ለአምስት ጊዜያት ተከናውኗል።
ኢዜአ፣ አዲስ አበባ መስከረም 30/2010