ዜና ዜና

ለሕዳሴው ግድብ በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ይሰራል

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ ማቀዱን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በ2010 በጀት ዓመት ዕቅዱ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ መክሯል።

የጽሕፈት ቤቱ የፕሮጀክት ማኔጅመንትና የአካባቢ ጥበቃ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተካ እቅዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ጽህፈት ቤቱ በተያዘው ዓመት የሕብረተሰቡን ተሳትፎ ይበልጥ በማሳደግ ገቢ የማሰባሰብ ተግባር ላይ ያተኩራል።

ገቢው ለዚሁ ተብሎ በሚዘጋጁ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች፣ከቦንድ ሽያጭ እና መሰል የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት በ2010 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እንደሚያሰባስብም ጠቁመዋል።

የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የማሳደግ ሥራ፤ በተለይም የአርሶና አርብቶ አደሩን፣ የባለኃብቱንና የዲያስፖራውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ከፍ ማድረግ በቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት "በተያዘው ዓመት በተለይ ባለኃብቱ ለግድቡ ግንባታ የገባውን ቃል ሙሉ ለሙሉ እንዲፈጽም የማስተባበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል" ።

ባለኃብቱ ለግንባታው የገባውን ቃል በወቅቱ ለማስረከብ በሥራ መደራረብ ጫና ክፍተቶች እንደነበሩ አንስተው፤ ይህንኑ ተግዳሮት ለማቃለልም ጽህፈት ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ይንቀሳቀሳል ነው ያሉት።

በዘንድሮው ዓመት የዲያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግም የቶሞቦላ ሎተሪዎች እንደሚዘጋጁና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በኩልም እንደሚሸጡ ነው የገለጹት።

የግድቡ ግንባታ የሕዝብ ክንፍ አስተባባሪ የክብር አምባሳደር አቶ ሙኡዝ ገብረሕይወት እንዳሉት፤ ሕዝቡ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ተሳትፎ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

''ነገር ግን ይህ የተጠናከረ ተሳትፎ በተጀመረበት መልኩ እንዲቀጥልና ግንባታውም ከዳር እስኪደርስ ሕዝቡን የማስተባበር ሥራው በይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል'' ነው ያሉት።

የሲቪክ ማኅበራት ሊቀመንበር አቶ ነጋሽ ተክሉ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ተሳትፎ በተጠናከረ መልኩ ለማስኬድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ በተለይ የሲቪከ ማኅበራት ድርሻ አናሳ መሆኑን ነው የገለጹት ።

በመላው አገሪቱ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞች ያሉ ሲሆን፤ የሚጠበቅባቸውንና ወጥነት ያለውን ተሳትፎ በማድረጉ ረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ ነው ያሉት።

ከኢትዮጵ ሃይማኖቶች ጉባኤ የተወከሉት አቶ አዳነ ደቻሳ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ ዓመት ከቦንድ ሽያጭና ከሌሎች መስኮች ለማግኘት የታቀደውን ገቢ ለማሳደግ የ8100 የስልክ አጭር የጽሁፍ መልዕክትን ጨምሮ ሌሎችም አዳዲስ ሐሳቦች ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጱያ ዲያስፖራ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው፤ በውጭ የሚኖረው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግድቡን በተመለከተ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማሳደግ በተከታታይ የውይይት መድረኮች ሊዘጋጁ ይገባል ብለዋል።

ምክር ቤቱ በ2009 በጀት ዓመት ከመንግስት ሰራተኛው፣ ከዲያስፖራው፣ ከባለሃብቱና ከሕብረተሰቡ በቦንድ ሽያጭ፣ ሎተሪ፣ ከአጭር የጽሁፍ መልዕክትና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለግድቡ ግንባታ አሰባስቧል።

በአጠቃላይ ከመላው ኢትዮጵያዊያን የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ዓመት አንስቶ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን 2010 በጀት ዓመት ደግሞ የሕብረተሰቡን ድጋፍ ወደ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ እቅድ ተቀምጧል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሕዝቡ በበጎ ፈቃደኝነት በሚሰበሰብ ገንዘብና በመንግስት ወጪ በመካሄድ ላይ ሲሆን ግንባታው 60 በመቶ ተጠናቋል።

ኢዜአ፣ አዲስ አበባ መስከረም 30/2010