ዜና ዜና

ማዕከሉ በሞቃታማ አካባቢዎች በሰፋፊ እርሻዎች መልማት የሚችሉ የሱፍ ዝርያዎችን እያላመደ ነው፡፡

የጎንደር ግብርና ምርምር ማእከል ሞቃታማ ስነ ምህዳር ባላቸውና በሰፋፊ እርሻዎች መልማት የሚችሉ የሱፍ ዝርያዎችን እያላመደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ማእከሉ በመተማ ወረዳ በሚገኘው ሰርቶ ማሳያው ለመጀመሪያ ጊዜ እያላመዳቸው የሚገኙትን የሱፍ ዝርያዎች ሰሞኑን ለአርሶ አደሮችና ለባለሀብቶች አስተዋውቋል፡፡

የማእከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጸዳሉ ጀንበር እንደተናገሩት የሱፍ ዝርያዎቹ ለሀገር ውስጥ የዘይት አምራቾች ግብአት የሚውሉና ከውጪ ሀገር የሚገባውን የሱፍ ዘይት መተካት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

ማእከሉ በመተማ አካባቢ ባቋቋመው የምርምር ጣቢያ ላለፉት ሁለት አመታት በአምስት የሱፍ ዝርያዎች ላይ የዝርያ መረጣና የማላመድ ስራዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

በምርምር ጣቢያው ዝርያዎቹ በሽታንና ተባይ የመቋቋም ብቃታቸውን እንዲሁም ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚነታቸውን በምርምር የመፈተሸ ስራ ተከናውኗል፡፡

የሱፍ ዝርያዎቹ እስከ 30 በመቶ የዘይት ምርት የመስጠት ብቃት ሲኖራቸው ምርታማነታቸውም በሄክታር 20 ኩንታል የሚደርስ ነው፡፡

በዞኑ ምእራባዊ ቆላማ አካባቢዎች በሰፋፊ እርሻዎች ላይ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች የሱፍ ዝርያዎቹን ቢያለሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

ማእከሉ በቀጣዩ አመት የሱፍ ዝርያዎቹን ለአርሶ አደሩና ለባለሀብቶች በስፋት በማስተዋወቅ ዝርያዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ ለማመቻቸት ተዘጋጅቷል፡፡

የሱፍ ዝርያዎቹ በቆላማ አካባቢዎች ከሰሊጥ ቀጥሎ አማራጭ የቅባት ሰብል ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ማእከሉ ለግብርና ምርታማነት መጨመር እያደረገ ባለው ጥረትም ባለፈው አመት ጎንደር አንድ የተባለና በሄክታር 10 ኩንታል ምርት የሚሰጥ የሰሊጥ ዝርያ በምርምር በማፍለቅ ለተጠቃሚዎች አድርሷል ።

"በአሁኑ ወቅት ሰሊጥ አምራቾች ዝርያውን እያለሙ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በቅመማ ቅመም ዘርፍ ሁለት የነጭ አዝሙድ ዝርያዎችን በምርምር ያፈለቀው ማእከሉ ቅመም አምራች በሆኑ በአለፋና ጣቁሳ ወረዳዎች ዝርያዎቹን የማባዛት ስራ ማካሄድ ጀምሯል፡፡

በጉብኝቱ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ የመተማ አካባቢ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ታምራት ባዬና አቶ ቀናው ሙሉአለም በአካባቢው ከሰሊጥ ውጪ የሚለማ የቅባት ሰብል አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

''የምርምር ማእከሉ ያላመዳቸው የሱፍ ዝርያዎች ለአካባቢው ስነ ምህዳር ተስማሚነታቸው ከተረጋገጠ በቀጣዩ አመት ለማልማት ዝግጁ ነን'' ብለዋል፡፡

በዞኑ ምእራባዊ ቆላማ በሚባሉት በመተማ ቋራ ምእራብና ታች አርማጭሆ እንዲሁም ጠገዴ ወረዳዎች ለቅባት ሰብሎች ልማት ተስማሚ የሆነ ከ160ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እደሚገኝ ታውቋል።

  ጎንደር መስከረም 21/2010(ኢዜአ)