ዜና ዜና

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተራራማ አካባቢዎችን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያሳድግ የምርምርና ልማት ኢንስቲትዩት አቋቋመ

በትግራይ ክልል በህብረተሰቡ ነፃ የጉልበት ተሳትፎ የለሙ ተራራማና ተዳፋት አካባቢዎችን የሚሰጡትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችል የምርምርና ልማት ኢንስቲትዩት ማቋቋሙን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡

በዩኒቨርስቲው የውሀና አከባቢ ኢንስቲዩቱት ዳሬክተር ዶክተር እያሱ ያዘው ለኢዜአ እንደገለፀት 63 በመቶ የሚሆነውን የክልሉ መሬት ተራራማና ተዳፋታማ ነው፡፡
በዚህም ክልሉ ከሚሸፍነው 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ለእርሻ አገልግሎት የሚውለው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ብቻ ነው፡፡
ቀሪውና ሰፊው መሬት ከእርሻ አገልግሎት ውጭ በመሆን የረባ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት ተራራማ አከባቢዎች ከፍተኛ የአፈር መከላት የሚታይባቸውና የተመናመነ የደን ሽፋን የነበራቸው በመሆኑ በሜዳማው የእርሻ መሬት የጎርፍ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
''የክልሉ ህብረተሰብ ከ20 ዓመት በላይ ባካሄደው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ከተራራዎቹ ተንደርድሮ ይወርድ የነበረው ጎርፍ አሁን ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ አድርሷል'' ብለዋል፡፡

በህብረተሰቡ ጠንካራ ጥረት ተራራዎቹ መልማት በመጀመራቸው ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ እየተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ተራራማና ተዳፋት ቦታዎች የበለጠ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የምርምርና ልማት ኢንስቲትዩት አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

በተራራዎች ለእርሻ አገልግሎት ፣ ለቱሪዝም ፣ ለኮንስትራክሽንና ለማአድን አገልግሎት የሚውል ቦታዎችን በምርምርና ጥናት የመለየት ስራ እንደሚያከናውን ተናግረዋል፡፡
በወረዳ ደረጃም የኢኮ ቱሪዝም፣ የተራራ እርሻና የማእድን ጣቢያዎች በማቋቋምና ዓለም አቀፍን ልምድ በማምጣት ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የእፅዋት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር እምሩ ብርሀነ በበኩላቸው ለደን ሀብት ፣ ለንብ ማነብ ፣ ለውሀ ባንክ ፣ ለእርሻና ለቱሪዝም አገልግሎት መዋል የሚገባቸው ተራራዎች በምርምር የመለየት ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ለወጣቶች የተከፋፈሉ ተራራዎችም ምን ያህል እየተጠቀሙበት እንደሆነ፣ ለየትኛው የልማት ዘርፍ ቢውል የተሻለ ጥቅም እንደሚሰጥ የመለየት ስራም ኢንስቲትዩቱ እንደሚያከናውን አስታውቀዋል፡፡

መቀሌ መስከረም 13/2010 (ኢዜአ)