ዜና ዜና

በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የመሰረተ ልማት ሟሟላት ተግባር የሚበረታታ ነው - ጀርሚይ ላፍሮይ

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ መንግሥት እያከናወነ ያለው የመሰረተ ልማት ሟሟላት ሥራ የሚደነቅ መሆኑን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮጵያ የንግድ መልዕክተኛ ገለፁ።

የተሬዛ ሜይ የኢትዮጵያ የንግድ መልዕክተኛ ጀርሚይ ላፍሮይ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ጀርሚይ ላፍሮይ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በአገሪቱ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራን ለማሳለጥ መንግሥት ምቹ ማዕቀፍ መፍጠር መቻሉ የሚበረታታ ነው።

የአገሪቱ የመሰረተ ልማትና የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እንዲሁም በአነስተኛ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መኖሩ ይህንኑ የሚያመላክት መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህ እንቅስቃሴ ግዙፍ ኩባንያዎችን ወደ አገሪቱ ለመሳብና ኢንቨስትመንት እንዲያካሂዱ ለማስቻል እንደሚረዳ ነው የጠቆሙት።

"እንግሊዝም ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲጎለብት ትፈልጋለች፣ ለዚህም ነው እንግሊዝ የንግድ ልዑክ ያስፈለጋት" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ያሉትን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ማስተዋወቅና ኩባንያዎቹ በቅጡ እንዲረዱት ማድረግ በቀጣይ በሥፋት የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ ለውጭ የሚቀርቡ ምርቶችን በመጠን እንጨምሩ ከማድረግ በዘለለ የሥራ እድል መፍጠር ላይም አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ጎን ለጎንም የንግድ ግንኙነትን ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩና ይህም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ምጣኔ ሚዛን ለማቅናት እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

በአገሪቱ የሚካሄዱት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና መንግሥት ከኋላ ቀር የግብርና ዘርፍ ወደ ንግድ ተኮር ግብርና ከዛም ወደ ምግብ ማቀነባበሪያ የሚሰሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መሸጋገሩን አሞካሽተዋል።

ያም ሆኖ የግብርና ዘርፉ በደንብ ቢሰራበት አሁን ከሚያመርተው የግብርና ውጤቶች በላይ ከፍተኛ ምርት መሰብሰብ እንደሚችል አስታውቀዋል።

አገራቸውም በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖራት ግንኙነት በግብርና ዘርፍ ላይ በጋራ ለመስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በባቡር መስመር ዝርጋታ፣ በአየር መንገድ፣ በአገልግሎት ዘርፍና በምግብ ማሸግ ሥራ ሁለቱ አገራት ተባብረው እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

አገራቸው የኢትዮጵያን የኃይል ዘርፍ ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗንና ኢትዮጵያም በቅርቡ የአፍሪካ የኃይል ቋት እንደምትሆን ገልጸዋል። 

"ኢትዮጵያ በሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ላይ በመሥራት ቀደሚ አገር ናት፣ ይህንንም እናደንቃለን፣ በዚህም ላይ በጋራ መሥራት እንፈልጋለን" ብለዋል መልዕክተኛው

አዲስ አበባ መስከረም 13/2010 /ኢዜአ/