ዜና ዜና

የለውጥ ኃይል የሆነው ወጣት ለአገሩ ሠላም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል

የኢትዮጵያ ህዳሴ የለውጥ ኃይል የሆነው ወጣት ለአገር ሠላም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ርስቱ ይርዳው አሳሰቡ።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) አባላት ወጣቶች የድርጅቱን 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በፓናል ውይይት አክብረዋል።

ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፤ የወጣቶች ተጠቃሚነት በፍጥነት ሊረጋገጥ የሚችለው አገር ሠላም ሲሆን ብቻ ነው።

"በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ ለሠላም ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ አለበት" ነው ያሉት።

ደኢህዴን ባለፉት 25 ዓመታት የክልሉን ወጣቶች በተጨባጭ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ያወሱት ሚኒስትሩ ፤ በጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የተፈጠረውን የሥራ እድል ለአብነት ጠቅሰዋል።

"ድርጅቱ ይህን ስኬት ያስመዘገበው በክልሉ ብሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ሠላምና ደህንነት በመረጋገጡ ነው"ብለዋል።

መንግስት ከከፍተኛ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በተጨማሪ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን በተለያዩ አካባቢዎች ለመገንባት ልዩ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ድርጅቱ በርካታ አኩሪ ድሎችን ቢያስመዘግብም ሙስና፣ ብልሹ አሠራሮችና የጠባብነት አመለካከትና ተግባር አሁንም ያልተሻገራቸው ችግሮች ናቸው" ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የእቅድ፣ ሪፖርትና ግብረ መልስ ኃላፊ አቶ ብሩክ ከድር ናቸው።

ድርጅቱ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ትኩረት መስጠት እንደሚገባውም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ወጣቶች በበኩላቸው የድርጅቱ መስራቾች መስዋዕትነት ከፍለው ያመጡትን ሠላም የአሁኑ ትውልድ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ ገልፀዋል።

ወጣት ኤልያስ ወንድሙ ትውልዱ የዴሞክራሲ መርሆች እንዲጎለብቱ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግሯል።

ለዴሞክራሲ መጎልበት እንቅፋት የሆኑትን ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመታገል ረገድ ወጣቱ የግንባር ቀደምትነት ሚና መጫወት ይጠበቅበታል ነው ያለው።

ወጣቶች ጥያቄዎቻቸውን በሠላማዊ መንገድና ህግን ተከትለው የማቅረብ ባህላቸውን ማዳበር እንደሚገባቸው አስተያየት የሰጠችው ደግሞ ወጣት ታደለች ደስታ ናት።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎችም እየተከበረ ነው።

አዲስ አበባ መስከረም 13/2010 /ኢዜአ/