ዜና ዜና

በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተመራ ልኡክ የአዋሽ ወንዝ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ጎበኘ

በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የተመራ ልኡክ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በተከሰተለው የጎርፍ አደጋ ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን እና ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ጎበኙ ።

ሰሞኑን በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ የተወሰኑ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በውሀ እንዲዋጡ አድርጓቸዋል።

በአዋሽ ወንዝ መሙላት ምክንያትም ወንዙን ተጠግተው የሚገኙ 12 ቀበሌዎች በጎርፍ የተጥለቀለቁ ሲሆን፥ በቀበሌዎቹ የሚኖሩ ሰዎችም ጉዳት ሳይደርስባቸው አካባቢያቸውን እንዲለቁ ተደርጓል።

በዛሬው እለትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ውርቅነህ ገበየሁ እና በኦሮሚያ ክልል መንግስት ካቢኔ የሚመራ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ልኡክ ስፍራው ድረስ በመሄድ በጎርፍ አደጋው ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም በጎርፍ አደጋ ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች አስፈላጊ የሆኑ እርዳታዎች ማለትም እንደ ልብስ፣ የምገብ እህል እና መድሃኒት እየተከፋፈለ መሆኑ መመልከት ተችሏል።

ወደፊትም በጎርፍ አደጋው ምከንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች መልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረግላቸው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጠል መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ አስታውቀዋል።
መስከረም 3፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ)