ዜና ዜና

በንብ ማነብ የሚገኝ ምርትን ለማሳደግ ወጣቶችና ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከንብ ማነብ ከምታገኘው ምርት ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ በሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችና ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ እየሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በንብ መንጋ ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን፤ አሁን ላይ 10 ሚሊዮን የሚደርሱ የንብ መንጋ እንዳላት ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

ሆኖም በንብ ማነብ ሥራ ላይ ባለው ዝቅተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ አገሪቷ ከንብ ማነብ ከምታገኘው ምርት  ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም እያገኘች አለመሆኑን ነው ሚኒስቴሩ የሚገልጸው።

በንብ ማነብና አያያዝና ጥራት ችግር አልያም ደግሞ በሚመረቱት ውስን የንብ ውጤቶች ላይ እሴት የመጨመርና የማሸግ ሥራ ላይ ያለው ውስንነትም ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል።

አገሪቷ በዓመት 500 ሺ ቶን ማር ማምረት የሚያስችል አቅም እያላት፤ በአሁን ወቅት ከ10 በመቶ በታች የሚሆን ማር ነው እያመረተች የምትገኘው።

ለምሳሌ ያክልም በተጠናቀቀው ባጀት ዓመት 444 ቶን ማር በማምረትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር  መገኘቱ ተጠቅሷል።

በመሆኑም ምርቱን ለማሳደግና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ፤ እሴት የተጨመረበት ማር ለገበያ ለማቅረብ አዳዲስ ስራ ፈላጊ ወጣቶችና ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉበት እየተሰራ መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብርኃቱ መለስ የሚናገሩት።

ይህ እቅድ እውን እንዲሆን ደግሞ መንግሥት ከመደበው የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ በዘርፉ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ወጣቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በዘርፉ ያሉ ባለኃብቶችም ሥራቸውን እንዲያስፋፉ የኢንቨስትመንት ማበረታቻውንም ጭምር በመፈተሽ ከቀረጥ ነጻ መሳሪያዎችን እንዲያስገቡ መፈቀዱን አስረድተዋል።

"ምርቱን እሴት አክሎበት ለገበያ ማቅረብ የሚችሉ አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየሰራን ነው" ብለዋል።

በሙከራ ደረጃም በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች በተመረጡ አራት ቦታዎችን ላይ የፓርኮቹ የመሰረተ ልማት ግንባታ መጀመራቸውን ያስረዱት ዶክተር መብርኃቱ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ፍላጎት ያላቸውን ባለሃብቶች የመለየትና ሼዶችን የመገንባት ስራ ይከናወናል ብለዋል።

በቀጣይ ዓመታት ደግሞ በአስራ ሰባት ቀጣናዎች ላይ የተቀናጁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንደሚካሄድ በመጠቆም።

በአሁኑ ወቅት መደበኛ በሚባለው የንብ ማነብ ሥራ ከአንድ ቀፎ ላይ በዓመት ሁለት ጊዜ በመቁረጥ፤ በአማካይ 25 ኪሎ ግራም ማር እየተሰበሰበ ይገኛል። 

ይሁን እንጂ የቴክኖሎጂዎች ግብዓቶችን በመጠቀም ከአንድ ቀፎ ላይ በዓመት ስምንት ጊዜ ማር በመቁረጥ፣ 80 ኪሎ ግራም ማር ማምረት እንደሚቻል ገልጸዋል።

በዚህም ረገድ የእነዚህ ባለሃብቶች ሚና በተለይም የእሴት ሰንሰለቱን በመጠቀም በምርቱ ሂደት ላይም አስተዋጽዖ እንደሚኖራቸው  ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል በጸረ-ውድድር ድርጊት ውስጥ በመግባት ምርቱን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል የጥራት ችግር በሚፈጥሩ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህም በዘርፉ ወንጀሎች የሚፈጽሙ ነጋዴዎች አስተማሪ በሆነ መልኩ ለመቅጣትና "በአኳያው የንግድ ሥርዓቱን ሕጋዊ በሆነ መልኩ ለመምራት ያግዛል" ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ንቦች ሊቀስሙት የሚችሉ ከ800 በላይ እጽዋት ባለቤት ከመሆኗ ባሻገር በአገሪቷ የሚካሄደው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ፣ "የንብ መንጋውን ከዚህ በላይ ያሳድጋል" የሚል ትንበያም አለ።

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010(ኢዜአ)