ዜና ዜና

በትግራይ ክልል የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስና ፍላጎቱን ለማርካት የሚደረገው ጥረት በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ልዑል ካሕሳይ እንደገለፁት በትግራይ ባለፈው የበጀት ዓመት መልካም አስተዳደርና ፍትህ ከማስፈን አኳያ ጥሩ የሚባል አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡

ቢሮው በፍትህ ስርዓቱ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ከ2 ሚሊዮን 400 ሺህ ለሚበልጥ ህዝብ የንቃተ ህግ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ አራጣ አበዳሪ፣ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከልን አስመልክቶ የተሰጠው ትምህርት ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በቢሮው ስር የሚገኘው የወሳኝ ኩነት አደረጃጀት በማጠናከርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ከ25 ሺህ በላይ አዲስ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተካሂዷል፡፡

ሆኖም በየጊዜው የሚወለዱ ህጻናትን በወሳኝ ኩነት የክብር መዝገብ ማስመዝገብ ስራ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩ ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

ይህም " ስራው የፍትህ ቢሮ ብቻ ተደርጎ በመታየቱና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው አለመስራታቸው የፈጠረው ችግር ነው "ብለዋል።

በቀጣይም የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ጥሩ መሻሻል ቢታይም በይግባኝና ሰበር ጉዳዮች አፈጻጸም ላይ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ ነው አቶ ልዑል ያመለከቱት።

እሳቸው እንዳሉት ቢሮው በየጊዜው የስራ ግምገማ በማካሄድ ችግሮችን ለመፍታት የተጓዘባቸው መንገዶች መልካም ናቸው፤ ሆኖም የመንግስትና ህዝብ ፍላጎት ከማሳካት አንፃር ክፍተቶች እንዳሉና ብዙ መስራትን ይጠይቃል፡፡

ከውሳኔዎች ፍትሃዊነትና ጥራት አንፃር የነበሩ እጥረቶችን በማስተካከል የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስና ፍላጎቱን ለማርካት የሚደረገው ጥረት በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በክልል ደረጃ አንገብጋቢ የሆኑ ችግሮች ተብለው የተለዩትን የመሬት ወረራ፣ ህገወጥ ግንባታ፣ አስገድዶ መድፈርና አራጣ አበዳሪነት ለመከላከል በትኩረት ይሰራል ተብሏል፡፡

የወንጀል ምርመራ ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ልዑል ግርማይ በበኩላቸው "ወንጀለኞችን ተከታትለን በመያዝ፣ድርጊቱን በመመርመርና በማጣራት በጊዜው ወደ ሚመለከተው የህግ አካል እያቀርብን እንገኛለን "ብለዋል።

በእውነት ላይ ተመስርቶ የምስክርነት ቃልን መስጠት ወንጀል እንዳይስፋፋ የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አማኑኤል ኪዳኔ ናቸው፡፡

" የፍትህ አካላት እውነቱን ለማውጣት የሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት በሚሆኑ ምስክሮች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል"ብለዋል፡፡
ኢዜአ፤መስከረም2/2010