ዜና ዜና

የጤና ተቋማት የህክምና መሳሪያና መድሃኒት ሲገዙ ቀድመው እንዲከፍሉ የሚያስገድድ የግዥ ስርዓት ሊዘረጋ ነው

የጤና ተቋማት የህክምና መሳሪያዎችንና መድሃኒቶችን ሲገዙ ክፍያ ቀድመው እንዲፈፅሙ የሚያስገድድ አዲስ የግዥ ስርዓት ሊዘረጋ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለፀ።

ከዚህ ቀደም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ሁሉም የጤና ተቋማት የህክምና መሳሪያዎችን እና መድሀኒቶችን ግዥ የሚፈፅሙበት ስርዓት በዱቤ ነበር።

መድሀኒቶቹን የመድሀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ በራሱ ገንዘብ ገዝቶ በማስመጣት ለጤና ተቋማቱ ጥያቄ ሲያቀርቡለት ሲሸጥ ቆይቷል።

መድሀኒቶቹ ቀድመው ጥያቄ ላቀረቡ እና ክፍያውን እጅ በእጅ የሚፈፅሙ የግል ጤና ተቋማትን እንደሚያስቀድም ፥ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብረሀን ተናግረዋል።

የህክምና መሳሪያዎቹም ቢሆን በዱቤ ከመምጣታቸው ባሻገር፥ አስመጪ ኩባንያዎቹ ከጨረታ ስርዓቱ ጀምሮ ላመጡት መሳሪያ ምንም አይነት ተጠያቂነት እና ዋስትና የሌለው አሰራርን ሲከተሉ መቆየታቸውን ነው ሚኒስትሩ የሚናገሩት።

በግዥ ስርዓቱ ላይ በነበሩ ክፍተቶች ምክንያት በየተቋማቱ የመድሃኒት እጥረት ያጋጥም የነበረ ሲሆን፥ የህክምና መሳሪያዎች ብልሽት ሲገጥማቸው የስራ መቆም ጭምር ሲፈጥር መቆየቱን ፕሮፌሰር ይፍሩ ገልፀዋል።

የመድሀኒቶችና የህክምና መሳሪያዎች ግዥ ስርዓት ለማሻሻልና ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንቅስቃሴ ጀምሯል።

በዱቤ የነበረውን የግዥ ስርዓትን ሙሉ በሙሉ ቀይሮ አዲስ ሰርዓት ለመዘርጋት ዝግጅት ተደርጓል ነው የተባለው።

በአዲሱ አሰራርም የመድሀኒት ፈንድ እና አቅርቦት ኤጀንሲ ያስመጣውን መድሃኒት ሁሉም ጤና ተቋማት የሚፈልጉትን መድሃኒት ቀድመው ባዘዙት መሰረት፥ ቅድሚያ ክፍያ በመፈፀም እንደሚገዙ ፕሮፌሰር ይፍሩ ጠቁመዋል።

የህክምና መሳሪያ አስመጪዎች ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረው ተጠያቂነት እና ዋስትና የሌለው የግዥ ስርዓት ተቀይሮ፥ መሳሪያዎቹን ማስመጣትና ዋስትና ከመስጠት ባለፈ የሚያስመጧቸው መሳሪያዎች መስፈርት በአዲሱ አሰራር ተለይተው ተቀምጠዋል ነው ያሉት።

ኩባንያዎች ላቀረቡት መሳርያ ተጠያቂ የሚሆኑበት እና ከ3 እስከ 4 ዓመት የሚደርስ የዋስትና ውል እንዲፈፅሙ የሚያደርግ ነው።

መሳሪያዎቹ የዓለም ጤና ድርጅት መስፈርትን የሚያሟሉ፣ የአሜሪካ የምግብ እና መድሀኒት ተቋም እውቅና የሰጣቸው እና የአውሮፓ ህብረት መመዘኛ የሚያሟሉ መሆን አለባቸው የሚሉት ዋና መስፈርት ናቸው ብለዋል።

አቅራቢዎቹ ለሚያቀርቡት መሳሪያ ተጠያቂ ለመሆን ውል የሚያስሩበት አሰራር መዘርጋቱ ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረውን ክፍተት እንደሚቀርፍ ተነግሯል።

አዲሱ አሰራር የጤና ተቋማቱ ጥራትና ጊዜን ያማከለ አገልግሎት እንዲኖር ስለሚያስችል በህክምናው ላይ ትልቅ ለውጥን እንደሚያመጣ ታምኖበታል።

አሰራሩ ሁሉም ክልሎችና የጤና ተቋማት እንዲያውቁት ከተደረገ በኋላ በቀጣይ ጊዜ ተግባራዊ ይሆናልም ተብሏል።

 

  አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ)