ዜና ዜና

ከሁለቱ ሀገራት የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ ስራ ጀመረ

የሁለትዮሽ ትብብር - ላላቀ የሴቶችና ህጻናት ተሳትፎና ተጠቃሚነት
የኢፌዴሪ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ከሩዋንዳ መንግስት የስርዓተ ጾታና የቤተሰብ ጉዳይ ሚኒስቴር በትብብር ለመስራት በተደረሰው መግባባት መሰረት ከሁለቱም ሀገራት የተውጣጡ የቴክኒክ ኮሚቴ ስራ መጀመራቸው ተገለጸ፡፡

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ደሚቱ ሃምቢሳ ከሁለቱ ሃገራት የተውጣጡ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት የግንኙነት መድረክ ላይ እንደገለፁት ቀደም ሲል በሁለቱ ሃገራት መንግስታት በተፈረመው የጋራ መግባቢያ ሰነድ መሰረት ሁለቱ ሃገራት በሴቶችና ህጻናት ተጠቃሚነት ዘርፍና በስርዓተ ጾታ እኩልነት ዙሪያ ላይ ትኩረት በማድረግ በየሀገራቱ ያሉትን የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር መመሪያዎች ተፈጻሚ ከማድረግ አኳያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ በመፍታት የቴክኒክ ኮሚቴው ሚና የጎላ ነው፡፡

በዋናነትም በሁለቱም ሃገራት በተገኙ ስኬቶች ዙሪያ የልምድ ልውውጦችን በማስፋት ረገድ ከቴክኒክ ኮሚቴው ብዙ እንደሚጠበቅ የጠቀሱት ሚኒስትሯ የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዘላቂነት በማረጋገጥና የህጻናትን መብትና ደህንነት በማስከበር ረገድ ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል በባለቤትነት እንዲንቀሳቀስና በሁለቱ ሃገራት መካከል የሰመረ ግንኙነት እንዲኖር ቴክኒክ ኮሚቴው ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የቴክኒክ ኮሚቴው በግንኙነት መድረኩ ላይ ያዘጋጀውን የቀጣይ አምስት አመት የድርጊት መርሃ ግብር በጋራ ያጸደቀ ሲሆን ወደ ተግባር ለመግባት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

መረጃው ያደረሰን የኢፌዴሪ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡

መስከረም 2/2010