ዜና ዜና

አለማቀፉ ማህበረሰብ ለሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት ድጋፍ እነዲያደርግ ተጠየቀ

ሶማሊያንና ደቡብ ሱዳንን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት አለማቀፉ ማህበረሰብ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠየቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በቀጠናው ስላለው የሰላም ሁኔታ ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት በጽህፈት ቤታቸው ገለጻ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ሱዳንን መልሶ ግንባታ በተመለከተና በሶማሊያ ስለሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አሰከባሪ ሃይል (አሚሶም) በዋናነት ገለጻ አድርገዋል።

ውይይቱን የተከታተሉት በጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ዶክተር ተቀዳ አለሙ እንዳሉት፤ አለማቀፉ ማህበረሰብ በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አሰከባሪ ሃይል (አሚሶምን) በፋይናንስ የመደገፉ ሂደት እየቀነሰ መጥቷል።

በቀጣናው ሰላምን የማስፈኑ ጉዳይ ለአፍሪካ ብቻ የሚተው ባለመሆኑ አለማቀፍ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ በዘላቂነት በማድረግ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጸጥታው ምክር ቤት አባላት መልዕክት እንዳስተላለፉም ተናግረዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት አለም አቀፍ ተቋም ከመሆኑ አኳያ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ጨምረው መግለጻቸውንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደቡብ ሱዳንን ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለስ በኩል የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በቅርበት ከሚከታተለው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስት (ኢጋድ) ጋር በቅርበት እንዲሰራ መጠየቃቸውንም ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።

ኢጋድ ደቡብ ሱዳን ወደ ሰላም እና መረጋጋት እንድትመለስ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራ መገለፁንም ተናግረዋል።

አባላቱ ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ እንዳደነቁም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት ለአንድ ወር በኢትዮጵያ ፕሬዝዳንትነት ይመራል።

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009/ኢዜአ/