ዜና ዜና

በሙስና የተጠረጠሩ የስራ ሃላፊዎችና ባለሃብቶችን ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለፀ

መንግስት በአቋራጭ መክበርን ዋነኛ ስራቸው አድርገው በሚንቀሳቀሱ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጥገኛ ባለሀብቶችና ደላሎችን ለህግ ማቅረቡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ በየወቅቱ የሚያጋጥሙ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ፈተናዎችን ለመከላከል ሙስና የሚፈፅሙ ወንጀለኞችን ለህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብሏል።

በቅርቡም በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ በስኳር ኮርፖሬሽን፣ በፌደራልና በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንና በባህር ትራንዚትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ሲሰሩ የነበሩ የስራ ሃላፊዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያለው።

ከሙስና ወንጀሉ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ባለሃብቶችና ደላሎች ላይም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ጠቅሷል።

አንዳንድ ወገኖች የፀረ ሙስና ትግሉን ዋጋ ለማሳጣት እየሞከሩ ቢሆንም፥ መንግስት እሴት ሳይጨምሩ በአቋራጭ መክበርን ዋነኛ ስራቸው ያደረጉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ጥገኛ ባለሃብቶችና ደላሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ ማተኮሩን ተናግረዋል።

የመንግስትና የህዝብን ሃብት የሚመዘብሩ ግለሰቦች ከገቡበት ቦታ ተይዘው ለህግ እንደሚቀርቡም በአፅንኦት በመግለጫው ላይ ቀርቧል።

በአንፃሩ የተጀመረውን ልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከዳር ለማድረስ፥ የሚጥሩ የመንግስት አመራሮች፣ ሰራተኞችና ታዳጊ ልማታዊ ባለሃብቶች ከመንግስት ጎን ሆነው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሷል።

በቀጣይም በሚካሄዱ የፀረ ሙስና ትግሎችም ተሳተፏቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል ተብሏል።

የፀረ ሙስና ትግሉ ዋነኛ ዓላማ የመንግስት ስልጣን የህዝብ ማገልገያ መሳሪያ እንጅ የግለሰቦች የሃብት ማከማቻ እንዳይሆን ለመከላከል መሆኑም ነው የተገለፀው።

ስልጣናቸውን መከታ አድርገው ከጥገኛ ባለሃብቱ ጋር በጥቅም በመተሳሰር፥ በሀገሪቱ እድገት ላይ ከባድ ጉዳት እያስከተሉ በሚገኙ አካላት ላይ ያነጣጠረ እርምጃ ለመውሰድ ህብረተሰቡ በጥቆማና በማስረጃነት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል።

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)