ዜና ዜና

የኢትዮጵያ የሰላም ማስጠበቅ ተልዕኮ ለአፍሪካ አገራት አብነት ነው- በተመድ የስዊዲንና ብሪታንያ ተወካይ አምባሳደሮች

በአዲስ አበባ ዛሬ በተጀመረው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት እና በአፍሪካ ህብረት ሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት የጋራ ምክክር ለመሳተፍ ኢትዮዽያ የገቡት የብሪታንያ እና ስዊዲን ተወካይ አምባሳደሮች፥ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እየተወጣች ያለችው ሰላም የማስጠበቅ ተልዕኮ ለተቀሩት ሀገራት አብነት የሚሆን ነው ብሏል።

በተመድ የስዊዲኑ ተወካይ አምባሳደር ትናንት አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ እንደተናገሩት ኢትዮጵያና ስዊድን ያላቸው ግንኙነት በማጠናከር እና በአሁኑ ወቅት በፀጥታው ምክር ቤት ሁለቱ ሀገራት በአንድ ላይ ሆነው የተመድን እና የአፍሪካ ህብረትን ግንኙነት ለማጠናከር ይሰራሉ።

የብሪታንያው ተወካይ አምባሳደር ጆናታንም በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮዽያ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ እያደረገችው ያለው የሰላም ማስክበር ተልዕኮ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ያሉት አምባሳደር ጆናታን፥ በአሁኑ ወቅት ሁለንተናዊ ለውጥ የሚታይባት ሀገር ሆናለች ብሏል።

ይህ አካሄድ ደግሞ ለበርካታ ሀገራት መልካም ተምሳሌት በመሆኑ ብሪታንያ ለኢትዮዽያ ድጋፏን እንደምትሰጥ በማረጋገጥ፥ "እኔም በተራዬ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እሰራለሁ" በማለት አምባሳደር ጆናታን ገልፀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት 15ቱን ቋሚ እና ተለዋጭ አባል ሀገራት ወክለው አዲስ አበባ የሚገኙ አምባሳደሮች፥ ኢትዮዽያ አፍሪካዊያንን በማስተባበር የአህጉሪቷ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ የምታካሂዳቸው ስራዎች ዋጋ ሊሰጠው ይገባል የሚል አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።

  አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)