ዜና ዜና

ኢትዮጵያ ያላት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በአለም አቀፍ መድረኮች ተደማጭነቷን አሳድጎታል--- አቶ መለስ አለም

ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገው የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ የሀገቱን መልካም ገጽታ በመገንባት በአለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተደማጭነት ማሳደግ እንዳስቻላት የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም  እንደገለጹት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ግብ ሀገሪቱ ለጀመረችው የሰላም ፣የዲሞክራሲና ልማት ጥረት በገንዘብ፣ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ መስኮች ድጋፍ ማግኘት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በሀገሪቱ እየታየ ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይ እንዲሆን ባለሀብቶችን በመሳብ ለግብርናና እሴት ተጨምሮ የሚላኩ ምርቶች ገበያ ለማፈላለግ የሚረዳ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማምጣት ዋና የዲፕሎማሲው አቅጣጫ ነው፡፡

የበርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት ሰላም ለማስከበር ባደረገው ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡

ቃለ አቀባዩ እንዳመለከቱት ከኮንጎና ኮሪያ በተጨማሪ ባለፉት አስርት ዓመታት ከላይቤሪያ እስከ ሩዋንዳ ከብሩንዲ እስከ ሱዳን የሰላም አስከባሪ ሀይል ልካለች፡፡

"በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላም አስከባሪ ሀይል ከሚልኩ ሀገራት ሁለተኛ በአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚዋ ናት ብለዋል"

ይህም ለሀገሪቱ ትልቁ የስኬት ማሳያና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የሰላም አጋርና የሌሎችን እንባ የምታብስ ሀገር መሆኗን በተግባር ማስመስከሯን ጠቅሰዋል፡፡

"አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ መዲና ናት የሚባለው እንዲሁ አይደለም "ያሉት ቃል አቀባዩ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የባለብዙ መድረኮች ላላት ሚና የሰጣት ዕውቅና ተደርጎ እንደሚወሰድም አመልክተዋል፡፡

በእነዚህና በሌሎችም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ያከናወነችው ተግባራት በአለም መድረክ ተሰሚነቷን በማሳደግ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እንድትሆን እንዳደረጋት ጠቁመዋል፡፡

ቃለ አቀባዩ እንዳስረዱት ከወራት በፊት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም የአለም የጤና ድርጅትን በዋና ሊቀመንበርነት እንዲመሩ  የመመረጣቸው ምክንያት በአህጉራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በምታቀርበው ሀሳብ ተጽእኖ መፍጠር በመቻሏ ነው፡፡

"ሀገራችን  በአለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፤  ብዙ ሀገራትም ለእኛ ቢሆን  ብለው እንዲመኙ አድርጓል "ብለዋል፡፡

በአጎራባች ሀገራት መካከል ትብብር ማድረግ የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ያመለከቱት አቶ መለስ የሀገራትን ትስስር ለማጠናከር በመሰረተ ልማት የማገናኘት ስራ መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያን ከኬንያ ጋር የሚያገናኝ የአስፋልት መንገድ እስከ ሞያሌ መጠናቀቁን ከሱዳንም ጋር በተመሳሳይ በመተማ በኩል መገናኘት እንደተቻለና ከጅቡቲ ጋር በመንገድም በባቡርም ማስተሳሰር ተችሏል፡፡

ይህም በሀገራቱ መካከል የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል እንደ አቶ መለስ ገለጻ፡፡

ኢትዮጵያ ለወጭና ለገቢ ንግድ ከጅቡቲ ጋር ባላት ስምምነት መሰረት የወደብ አገልግሎት እንደምትጠቀም አስታውሰው በተመሳሳይ የሰሜን ምዕራብ አካባቢ ላለው ደግሞ  የሱዳንን ወደብ መጠቀም የሚያስችላትን ስምምነት በቅርቡ መፈራረሟን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሁን ያለው ትውልድና አመራር ለሀገሩ ኃላፊነቱን መወጣትና አምባሳደር እንደሆነ ማሰብ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

  ሀዋሳ ጳጉሜ 1/2009(ኢዜአ)