ዜና ዜና

የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራጭ ሴቶች መድረክ (ኮከስ) ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርላማ ሴቶች መድረክ የ2009 እቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ትላንት በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

የተመራጭ ሴቶች መድረክ ሰብሳቢና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ እንደገለጹት መድረኩ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አባላት በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ በመንቀሳቀስ አደረጃጀቱን በማጠናከር ተሳትፎአቸውን ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ ነው።
"በተለይ በምክር ቤቱ ስራዎች በህግ ማውጣት፣ በክትትልና ቁጥጥር፣ በህዝብ ውክልናና በፓርላሜንታዊ ዲኘሎማሲ ስራዎች የሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡

በ2009 በጀት ዓመት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በመታገል ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አመለካከትን ለማጠናከር ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል።
"ለሴቶች የተሰጡትን ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮዎች ለመወጣትና ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል ብቃት ያላቸው የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አመራርና አባላት ለመፍጠር ተሞክሯል ነው" ያሉት ወይዘሮ ሽታዬ ።

በትግራይ፣በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተደራጁ የሴቶች ኮከስ ስራዎች የተገኙትን ምርጥ ተሞክሮ በመቀመር የኮከሱ አባላትና ሌሎች አደረጃጀቶች እንዲተላለፉ ተደርጓል ።

እንደ ወይዘሮ ሽታዬ ገለፃ ኮከሱ ለሴቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት የሚያበረክተው ድርሻ የጐላ በመሆኑ በቀጣይ በሁሉም የኮከስ እንቅስቃሴ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
በተለይ በ2010 የአዲስ አበባና የአካባቢ ምርጫ የሚካሄድበት ወቅት በመሆኑ በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ይደረጋል ።

እንዲሁም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲፈጸም የአመራርና የተመራጭ ሴቶችን ሚና ለማጠናከር በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰው ማሞ በበኩላቸው የክልሉ ኮከስ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲቃለሉ ብሎም የሴት ምክር ቤት አባላትን ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አዳማ ነሃሴ 30/2009(ኢዜአ)