ዜና ዜና

ተምቹ ወደ ጤፍ መዛመት በመጀመሩ ይበልጥ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል-ሚኒስቴሩ

በበቆሎ ሰብል ላይ የተከተው ተምች ጤፍን ማጥቃት በመጀመሩ አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ መከላከል እንዳለበት የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ ተምቹን ጨምሮ የተለያዩ ተባዮችን ለመከላከል በተወሰዱ እርምጃዎችና በመኸር እንቅስቃሴው ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በሚኒስቴሩ የእጽዋት ጤና ቁጥጥር ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ወልደሐዋርያት አሰፋ እንደገለጹት የአሜሪካ መጤ ተምች ወደ አገሪቷ ከገባ ጀምሮ የተለያዩ የመከላከል ስልቶች ተቀይሰው ሲተገበሩ ቆይተዋል።

ተባዩ በስድስት በቆሎ አምራች ክልሎች ተከስቶ 685 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ማጥቃቱንም ተናግረዋል።

ተምቹን በባህላዊ ዘዴና በኬሚካል በመታገዝ መከላከል መቻሉን ጠቁመው ከዚሁ ወስጥ 56 በመቶ በባህላዊ፤ 44 በመቶ ደግሞ በጸረ ተባይ ኬሚካል በአጠቃላይ 94 በመቶ ስኬት መመዝገቡን አስታውቀዋል።

''ተባዩን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎች ጥሩ ውጤት ቢገኝባቸውም ሙሉ በመሉ መቆጣጠር ተችሏል ማለት አይደለም'' ያሉት ዳይሬክተሩ በአንዳንድ ቦታዎች በባህላዊ መንገድ ተምቹን የመከላከል ተግባሩ መቀዛቀዙን ጠቁመዋል።

እንዲያም ሆኖ በወላይታና ደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ተምቹ ከበቆሎ አልፎ ጤፍ ላይ መከሰቱን ገልጸው አርሶ አደሩ ቢያንስ በቀን ሁለት ጊዜ ማሳውን በማሰስ የመከላከል ስራውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

በባለሙያዎች የተባይ ልየታ ችግር ማጋጠሙ፣ ተምቹን በመከላከል ሒደት በተወሰኑ አካባቢዎች የመሰላቸት ሁኔታ መታየቱ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ 2 ዞኖችና 16 ወረዳዎች እንዲሁም በአማራ በ 2 ዞኖችና በ4 ወረዳዎች የቢጫ ዋግ የስንዴ በሽታ ተከስቶ የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ወልደሐዋርያት ተናግረዋል።

ዋጉን ለመከላከል ከመንግስትና የግል አቅራቢዎች 245 ሺህ ጸረ ፈንገስ ኬሚካል መሰራጩትን ገልጸዋል ፡፡

በሌላ ዜና በተያዘው መኸር 345 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ከዋና ዋና ሰብሎች ለመሰብሰብ መታቀዱን በሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ወንድአለ ሀብታሙ አስረድተዋል።

እቅዱን ለማሳካት ምርት የሚጨምሩ ተግባራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹት አቶ ወንድአለ አርሶ አደሩ ማሳውን ደጋግሞ እንዲያርስ መደረጉ፣በአግባቡ እንዲያርም ግንዛቤ መፈጠሩ እንዲሁም ሜካናይዝድ እርሻ እንዲተገብር መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከማዳበሪያ አቅርቦት አኳያም 13 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ መቅረቡን አብራርተዋል።
ኢዜአ፣ አዲስ አበባ ነሐሴ 25/2009