ዜና ዜና

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የቤንች ማጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደቡብ ክልል የቤንች ማጂ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በክልሉ የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ ከተዘዋወረባቸው አካባቢዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ ትናንት ከሸካ ወደ ቤንች ማጂ ዞን ሲገባ በዞኑ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

በዋንጫው አቀባበል ስነስርአቱ ላይ ከተገኙት የቤንች ማጂ ዞኑ ነዋሪዎች መካከል የአዲስ ከተማ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አቤል ዶርቴት  እንደገለጹት በጡረታ ከሚያገኙት ሁለት ሺህ ብር ቦንድ ገዝተዋል፡፡

በግድቡ ግንባታ ላይ የራሳቸውን አሻራ ማኖራቸው የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸውና ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

"ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በመላ ሀገሪቱ መዘዋወሩ ገቢ ከማስገኘት በላይ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ትልቅ ሚና ተጫውቷል" ያሉት ደግሞ የሕብረት ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኃብተማርያም ካዝንቴት ናቸው፡፡

ለዋንጫው አቀባበል ሲደረግ የ500 ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልጸው ፣ ይህን ድጋፋቸውን በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

የቤንች ማጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወንድሙ ገብሬ በበኩላቸው "ግድቡ እንዲጠናቀቅ ከታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የተሰጠው አደራ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ግድቡን ከፍጻሜ በማድረስ እንወጠዋለን " ብለዋል፡፡

ግድቡ በራስ አቅምና በሀገር ልጅ መገንባቱ በሕዝቡ ላይ የይቻላል መንፈስ ማስረጹንና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማከናወን እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ በዞኑ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ ዋንጫው በዞኑ በሚኖረው ቆይታ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ክልል ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው በበኩላቸው ፣ ዋንጫው እስካሁን በተዘዋወረባቸው የክልሉ ዞኖችና ሦስት ልዩ ወረዳዎች የተሰበሰበው ገቢ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ዋንጫው ከገቢ ማሰባሰብ ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ አንዲጠናከር በማድረግ በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ዋንጫው የቤንቺ ማጂ ዞን ቆይታውን ሲያጠናቅቅ ሃዋሳ ከተማን ጨምሮ በክልሉ አራት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በሚኖረው ቆይታ ከፍተኛ ገቢ ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

 ሚዛን ነሀሴ 10/2009(ኢዜአ)