ዜና ዜና

የህዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጫ ተርባይኑን ከጉዳት የሚከላከለው መሳሪያ ምርት ተጠናቀቀ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ተርባይኑን ከጉዳት የሚከላከለው ''ትራሽራክያ'' የተሰኘውን መሣርያ ማምረቱን የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ገለጸ።

''ትራሽራክያ'' የተሰኘው ይህ መሳሪያ ከግድቡ ወደ ተርባይኑ በሚሄደው ውሃ ውስጥ ድንጋይ፣ እንጨትና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮች ተቀላቅለው ተርባዩኑን እንዳይጎዱት የያደርግ ነው።

የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሃይል ማመንጨት ሲሸጋገር በድምሩ 16 ትራሽራክያ ወይም የሃይል ማመንጫ ተርባይን መከላከያ የሚያስፈልግ ሲሆን አሁን በኮርፖሬሽኑ የተጠናቀቀው ቀድመው ሃይል ለሚያመነጩት ሁለት ተርባይኖች ብቻ ነው።

በኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ ፖዎር ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ የተርባይን ፋብሪካ ኃላፊ መቶ አለቃ ፀጋይ ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ እንደገለጹት 50 ቶን ክብደትና 21 ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መሣሪያ የማምረቱ ሥራው ተጠናቋል።

በተርባይን ፋብሪካ የዲዛይን ክፍል ኃላፊ ኢንጅነር ቢንያም ወልደየስ እንደገለጹት በፋብሪካው የግድቡን የኤሌክትሮ መካኒካል አካላትን ዲዛይን በማድረግ የማምረት ሥራው እየተካሄደ ነው።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው የግድቡ የሲቪልና የመካኒካል ስራዎች በአማካሪው ኩባንያ በኩል የጥራት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

እያንዳንዱ የግድቡ የሃይድሮና ኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ከዲዛይኑ ጀምሮ የማምረት፣ የመገጣጠምና መትከል ስራዎች በአማካሪዎች በኩል የጥራት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው የግድቡን ጥራት ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የቴክኖሎጂ ሽግግሩን የተሟላ እንዲያደርገው እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ደብረፅዮን አስታውቀዋል።

ይህን ከማስፈፀም አኳያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በርካታ ግድቦችን በመስራት በዘርፉ ታዋቂነት ያተረፉ ባለሙያዎች መቀጠራቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በተሰራው የግድቡ የሲቪልና የመካኒካል ስራ ላይ የዲዛይን ለውጥ ማሻሻያ በማድረግ የግድቡን ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 6 ሺ 450 ሜጋዋት ከፍ እንዲል ተደርጓል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጀመር 5 ሺ 250 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲያመነጭ ታስቦ ቢሆንም በጊዜ ሒደት የተጨመረው 1 ሺ 200 ሜጋ ዋት ኃይል የበለስ፣የተከዜና የጊቤ ሁለት ግድቦች በጋራ የሚያመነጩትን ኃይል ይስተካከላል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 60 በመቶ ያህሉ መጠናቀቁ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2009/ኢዜአ/