ዜና ዜና

በኦሮሚያ ክልል በህገ ወጥ ማስረጃ ሲሰሩ የነበሩ ከ1ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ተገኙ

በኦሮሚያ ክልል በሀስተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲሰሩ የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች መገኘታቸውን የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

ከሐምሌ 15 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይሰሩ የነበሩ የመንግስት ሰራተኞቹ እራሳቸውን እንዲያጋልጡ በተሰጣቸው ዕድል መሰረት ሰራተኞቹ ራሳቸውን እያጋጡ ነው ተብሏል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰራተኞች በክልሉ ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ባሉ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች ውስጥ በሀስተኛ የትምህርት ማስረጃ እየሰሩ የሚገኙ ናቸው።

በዚህም ያለአግባብ የማይገባቸውን ጥቅም እያገኙና በማይመጥናቸው የስራ ደረጃ ላይ በመስራት ላይ የሚገኙ ናቸው ብለዋል።
በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን የሚያጋልጡ ሰራተኞችን ይቅርታ ተደርጎላቸው ከዚህ በፊት ባላቸው ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃና በሚመጥናቸው የስራ ቦታ የሚሰሩ ይሆናል።

"ከነሐሴ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ቢሮው በሚያደርገው ማጣራት ህጋዊ ያልሆነ መረጃ ይዞ በማገልግል ላይ ያሉ ሰራተኞች ከስራው እስከ መጨረሻ ድረስ ይባረራሉ ፤ እስከ አሁን በሀሰተኛ መረጃ ያገኙትን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ይመልሳሉ" ነው ያሉት ዶክተር ቢቂላ።

ብቁ እና ተገቢውን አገልግሎት ለተጋልጋዩ ህብረተሰብ መስጠት የሚችል ሰራተኛ ለመፍጠር በተያዘው አሰራር መሰረት የማጥራቱ ስራ እንደሚቀጥል ገልፀው በመጀመሪያ ወደ ቅጣት ያልተገባው ሰራተኛው ጥፋቱን አምኖ ራሱን እንዲያጋልጥ መሆኑን ተናግረዋል።

የማጣራቱ ስራ ከፖሊስ ጋር በመሆን ሰራተኛው የትምህርት ማስረጃ ያገኘበትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ምርመራ በመደረግ ላይ እንደሚገኙም ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።

በክልሉ ከ470 ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች ያሉ ሲሆን በክልል ባሉት ተቋማት፣በከተማ አስተዳደሮች፣በዞኖች፣ በወረዳ እና በመንግስት የልማት ድርጅት የሚሰሩ ናቸው።

አዲስ አበባ ነሀሴ 6/2009 (ኢዜአ)