ዜና ዜና

" የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሚቀረፍበት ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ ሲደርስና ግልጽነት ሲኖር ነው"- የኤፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

የህዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች ትክክለኛ መረጃ በመያዝ ተጠያቂነትና ግልጽነትን በማስፈን የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሙስና እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መታገል እንደሚገባቸው የኤፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚንስትር ክቡር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አሳስቡ፡፡

ሚንስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ለፌዴራል ተቋማት የህዝብ ግንኙነትና ለኮሙዩኒኬሽን ሃላፊዎች እንዲሁም ባለሙያዎች የ2010 ዓ.ም የስራ አቅጣጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ክቡር ሚንስትሩ አቅጣጫ ሲያስቀምጡ እንዳሉት ዜጎች ህገመንግስቱን አውቀው ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቻቸውን ተረድተው፣ ለመብቶቻቸው፣ ለእኩልነትና ለጋራ ተጠቃሚነታቸው እንዲቆሙ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መብታቸውን እንዲያውቁ ፣አውቀውም መብታቸውን እንዲያስከብሩ ፣ ራሳቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ ማድረግም በትኩረት ሊሰራበት ይገባል።

ሁሉም የየራሱን ተቋማት ሃላፊዎችና ሰራተኞች የሚገባቸውን እውቀት በህገ- መንግስቱ ላይ በአጠቃላይ በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ምን አይነት ሃገር መገንባት እንዳለብን ግንዛቤ እንዲይዙ፣ ሃገሪቱ የምትፈልገውንና የምትደርስበትን ዕድገት ተገንዝቦ በሚሄዱበት ሁሉ የሃገር ዲፕሎማቶች እንዲሆኑ ማድረግ ከኮሙዩኒኬተሮች የሚጠበቅ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዶክተር ነገሪ አክለው ሲያብራሩ የኮሙዩኒኬሽን ስራ የሀገር ገፅታ ግንባታን ከተቋማት እንዲነሳ ማድረግን ፣ መረጃዎች ግልፅና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆኑ ማድረግን፣ አዝማሚያዎች በሳይንሳዊ መልኩ መቀበልና ማዳመጥን ፤ጥናት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ችግር ፈቺ ጥናቶችን ማድረግን ፣ ትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ አዝማሚያዎችን መስራት ፣ልዩ ትኩረት የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት መስራትና ትክክለኛ የሚዲያ መርጣ ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡

ሚንስትሩ አያይዘውም ሁሉም ኮሙዩኒኬተሮች በተሰጣቸው ሃላፊነት በትክክል የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በማደራጀትና ለሚመለከተው አካል በወቅቱ የማድረስ ክፍተቶች የሚስተዋሉ በመሆኑን ይህ ችግር በፍጥነት መቀረፍ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ህብረተሰቡ ስለ ህገመንግስቱ፣ ስለ ዲሞክራሲያዊ መብት፣ ስለ ሰብአዊ መብት ያለው ዕውቀት ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው የሚለውን በጥናት ማረጋገጥም እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

አጠቃላይ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን በክላስተር ደረጃ እንዴት እንደተመራ ጥንካሬዎቹንና ድክመቶቹን የሁለት ክላስተሮች ማለትም የመሰረተ ልማትና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክላስተሮች የ2009 ዓ.ም የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማብራሪያ ተጠሰጥቶባቸዋል፡፡

ነሃሴ 4/2009