ዜና ዜና

ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ያስመዘገበችው ውጤት በዘርፉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያስችላል ተባለ

ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ያስመዘገበችው ውጤት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በዘርፉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደምትገኝ አመላካች ነው ተባለ ።

በአዲሱ ዓመት በመስኖ የሚለማውን መሬት በማስፋትና የተሳታፊ አርሶ አደሮችን ቁጥር በማሳደግ 469 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታውቋል ።

በሚኒስቴሩ የአነስተኛ መስኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ አወል ኤልያስ እንደገለፁት በ2009 ዓ.ም በሁለት ዙር በተካሄደው የመስኖ ልማት 370 ሚሊዮን 592 ሺህ 655 ኩንታል ምርት ተገኝቷል ።

ከሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆነው የዓመቱ ክንውን በመስኖ የሚለማውን መሬት ከማልማት ፣ የተሳታፊ አርሶአደሮችን ቁጥር ከማሳደግና ከተገኘው ምርት አንፃር ሲገመገም ከ95 በመቶ በላይ እቅዱን ማሳካት ተችሏል ።
በዓመቱ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመስኖ የለማ ሲሆን 7ሚሊዮን የሚጠጉ አርሶአደሮች በዘርፉ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል ።

በአዲሱ ዓመትም በመስኖ የሚለማው መሬት ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር በማስፋትና በመስኖ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥር 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በማድረስ 469 ሚሊዮን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በበኩላቸው በዓመቱ በመስኖ ልማት የተገኘው ውጤት በመሰረተ ልማት አውታሮች መስፋፋትና በፈፃሚው ፣ በአምራቹና በተጠቃሚው የአመለካከት ለውጥ የተገኘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የተገኘው ውጤት በዘርፉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በዘርፉ የተያዙ ግቦችን ማሳካት እንደሚቻል አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
''ዘርፉ ያልተቀረፉ ተግዳሮቶች አሉት'' ያሉት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ልዩ ረዳት አቶ ሰለሞን ዳኜ በበኩላቸው ''ኢትዮጵያ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ የሚያደርጋት እምቅ ሀብት ቢኖራትም ከአምራቹ ተጠቃሚነትና ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃር ሲገመገም ገና በዳዴ ላይ ያለ ነው'' ብለዋል ።

በአትክልት ፣ ፍራፍሬና የስራ ስር ዘር አቅርቦት ፣ በማዳበሪያ አጠቃቀምና በተቀናጀ የእሴት ሰንሰለት ምርቱ ወደ ገበያ በፍጥነት አለመድረስ ዋነኞቹ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
አምራቹ አንዱን ኪሎ ቲማቲም ከ5 ብር ባልበለጠ ዋጋ እየሸጠ በመሀል ያሉ ሃይሎች ግን አንዱን ኪሎ አዲስ አበባ ላይ 23 ብር በመሸጥ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም የሚያገኙበት የተበላሸ የግብይት ስርዓት መኖሩን አስረድተዋል ።

የሆርቲካልቸር ምርት በብዛትና በጥራት በማምረት ከራሳችን ተርፈን የውጪ ገበያውን መቆጣጠር የምንችልበት እድል እያለን የተቀነባበረና ያልተቀነባበረ የአትክልት ምርት ከውጭ በማስገባት በ2008 ዓ.ም ብቻ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ከሚገባው የተቀነባበረና ያልተቀነባበረ የአትክልት ምርት ቀይ ሽንኩርት ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ በተጠቀሰው ዓመት ከሱዳን ብቻ 77 ሺህ 432 ቶን ምርት ወደ አገራችን መግባቱን ገልፀዋል።
በዘርፉ የሚታዩትን ተግዳሮቶች በሙሉ በመፍታት ከዘርፉ ማግኘት ያለብንን ጥቅም ለማስከበር ለመጪዎቹ አስር ዓመታት ስራ ላይ የሚውል የሆርቲካልቸር ልማት ስትራተጂ መዘጋጀቱን ልዩ አማካሪው ተናግረዋል ።

ስትራተጂው ከ10 ዓመታት በኋላ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ፣ በዓለም ገበያ ብቁና ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ማቅረብ ፣ ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥርና ለምግብና ስነምግብ ዋስትና መረጋገጥ የላቀ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችልና ከቀዳሚ አምራችና ላኪ የአፍሪካ አገራት መካከል ተወዳዳሪ የሆነ የሆርቲካልቸር ዘርፍ የመገንባት ራእይ የያዘ ነው ተብሏል ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም በአፈር ለምነት ፣ በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃና በአነስተኛ መስኖ ልማት የተከናወኑ ስራዎች ለመገምገምና በ2010 ዓ.ም እቅድ ላይ ለመምከር በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት በመወያየት ላይ ነው ።

አዳማ ነሃሴ 3/2009 (ኢዜአ)