ዜና ዜና

የህዳሴው ግደብ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትና የሰላም ምንጭ መሆኑ ተገለፀ

በኢትዮጵውያን እና ትውልድ ኢትዮጵውያን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እውን እየሆነ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ሀገራዊ መግባባቱን በማጠናከር የልማት መሳሪያ እንደሆነ ተገለፀ።

ግድቡ ከዚህም አልፎ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ባለ ግንኙነት በትብብር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የመወዳጀት ብሎም የሰላም ምንጭ እንደሆም ነው የተገለፀው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አሰተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት 9ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ አከናውኗል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ጉባኤው ላይ በ2009 በጀት ዓመት የህዳሴው ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች፣ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎችን እና በጣና ሀይቅ ላይ ስለተከሰተው የእምቦጭ አረም ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በጉባኤው ላይም በ2009 በጀት ዓመት ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።

ከገቢ ማስገኛዎች ባሻገር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲያገኝ በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች የሚተላለፉ ዘገባዎችን መሰራታቸው ተገልጿል።

በተጨማሪም ታላላቅ የዓለም የመገናኛ ብዙሃን ስለ ግድቡ በቂ መረጃን እንዲያሰራጩ መደረጉ በሪፖርቱ ላይ ተነስቷል።

በጉባኤው ከገቢ ማስገኛው ስራው በተጓዳኝ ከአባይ ተፋሰስ ሀገራት ጋር ስላለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳይ ላይም ውይይት ተደርጓል።

የፐብሊክ ዲፕሎማሲው በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት እየሰራ አይደለም፤ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉ አስተያየቶች ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተዋል።

የፐብሊክ ዲፕሉማሲ ቡድኑ ከህዳሴው ግድብ ባሻገር በተለያዩ የሀገሪቱ ጉዳዮችም ላይ ገብቶ እንዲሰራ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑም ተጠቅሷል።

በተያያዘ የእምቦጭ አረምን ከጣና ሀይቅ አልፎ ጢስ አባይ ላይ እየተዛመተ በመሆኑ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ስጋት እንዳይሆን ትኩረት እንዲሰጠውም በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

የውሃ መስኖ እና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ ጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ጊዜም መንግስት አረሙን ማጥፋት በሚቻልበት ዙሪያ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የግንባታ ሂደት እና አሁን ያለበትን ደረጃ አስመልከተው ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ለምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም ከገቢ ማሰባሰብ እና ከፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 26፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)