ዜና ዜና

በአማራ ክልል የገጠርና የከተማ መሬት አስተዳደር ስርዓቱን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመምራት እየተሰራ ነው፡፡

በአማራ ክልል የገጠርና የከተማ መሬት አስተዳደር ስርዓቱን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመምራትና ለማስተዳደር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ገለፁ።

በባህር ዳር ከተማ ከ120 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ህንፃ ትናንት ተመርቆ ለአገልግሎት ተዘጋጅቷል።

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት በክልሉ መሬት በልዩ ትኩረት መዝግቦ በመያዝ ለሚፈለገው የልማት ስራ እንዲውል ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በተለይም የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነውን የገጠርና የከተማ የመሬት ሃብት በተጠናና በተደራጀ መንገድ ለይቶ በመመዝገብ ዘላቂነት ባለው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተተገበረ ይገኛል።

የዚህ ዘመናዊ ህንፃ መገንባትም መረጃዎችን በተደራጀ አግባብ በመያዝ ለዘላቂ የኢኮኖሚ ግንባታና ልማት እንዲውል ለሚደረገው ጥረት እገዛ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

የክልሉ መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ኃላፊ አቶ ፀጋ አራጌ በበኩላቸው የመሬት አሰራሩን ከልማዳዊ አተገባበር ለማላቀቅ በተከናወነው ተግባር ረጅም ርቀት መጓዝ ተችሏል።

''ተቋሙን በሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በተቋማዊ ግንባታ ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት በአጭር ጊዜ የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ የላቀ ሚና አለው'' ብለዋል።

ባለፉት ዓመታትም ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚበልጡ ባለይዞታ አርሶ አደሮች ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በመስጠት ባለቤትነቱን የማረጋገጥ ስራ ተከናውኗል፡፡

በአሁኑ ወቅትም 2ኛ ዙር የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠት መጀመሩን ጠቁመዋል።

በክልሉ ያለውን የመሬት ሃብት የአየር ላይ ፎቶ በማንሳት፣ ካዳስተር የመስራትና የቅየሳ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።

የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከ120 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው ባለ አራት ወለል ህንፃ የተጀመረውን ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ውጤታማ እንዲሆን የሚያግዝ መሆኑን አስታውቀዋል።

ህንፃው ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ክፍሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የተለያዩ ላቦራቶሪ የአይሲቲና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎችን የያዘ ነው።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡና ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለወጡ የሰሜን ወሎ፣ የሰሜን ሽዋና የምዕራብ ጎጃም ዞኖች የመኪናና የቁሳቁስ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ለሌሎች የቀድሞ የቢሮ አመራሮች እውቅና የተሰጠ ሲሆን በስነ ስርዓቱ ላይም የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ባህር ዳር ሀምሌ 9/2009(ኢዜአ)