ዜና ዜና

ኢትዮጵያ በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አምስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቀቀች

ኢትዮጵያ በዓለም ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 12 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በአምስተኛ ደረጃ አጠናቀቀች።

ለአምስት ቀናት በኬኒያ መዲና ናይሮቢ ሲካሄድ የቆየው የዓለም ከ18 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ተጠናቋል።

ዛሬ ከሰዓት በተካሄደው 3 ሺህ ሜትር የወንዶች ፍጻሜ ውድድር አትሌት ሰለሞን ባረጋ በአንደኝነት በማጠናቀቅ ለአገሩ አራተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

በበርካታ ተመልካች የተሞላው ካሳራኒ ስታዲየም አትሌት ሰለሞን በውድድሩ የመጨረሻ ዙር ከኬኒያውያን አትሌቶች ጋር ከፍተኛ ፉክክር አድርጓል።

አትሌት ሰለሞን ውድድሩን ለመጨረስም ሰባት ደቂቃ 47 ሰከንድ  ከ16 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የራሱን ሰዓት በማሻሻል ነው ያሸነፈው።

በዚሁ ውድድር ሁለተኛና ሶስተኛ ኬኒያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ለአገራቸው ማስገኘት ችለዋል።

ለሰለሞን ማሸነፍ እገዛ የነበረው ኢትዮጵያዊው አትሌት ምልኬሳ መንገሻ አራተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

በ800 ሜትር የሴቶች ፍጻሜ ውድድር አትሌት ሂሩት መሸሻ ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።

ለአምስተኛ ወርቅ ይጠበቅ የነበረው በሁለት ሺህ ሜትር የወንዶች መሰናክል የፍጻሜ ውድድር በኬኒያዎቹ የበላይነት ተጠናቋል።

በመጨረሻው ዙር በኬኒያዊያንና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ፉክክር የኬኒያ አትሌቶች አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

አትሌት አለሙ ኪቴሳ ደግሞ ውድድሩን በሦስተኝነት በማጠናቀቅ የመጨረኛውን የነሐስ ሜዳሊያ ለአገሩ ማስገኘት ችሏል።

ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ ሦስት ብርና አምስት ነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ኢትዮጵያ ከዓለም አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

በመሆኑም በአጠቃላይ የሜዳሊያ ብዛት ታሪክ ከፍተኛው ሜዳሊያ የተመዘገበበት ከመሆኑም በላይ በመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ውድድር ሆኗል።

በዚሁ ሻምፒዮና ደቡብ አፍሪካ በአምስት ወርቅ በሦስት ብርና በሁለት ነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ አስር ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ በመሆን አጠናቃለች።

ቻይና እና ኩባ በተመሳሳይ አምስት ወርቅና ሁለት ብር ያገኙ ቢሆንም ቻይና አራት ነሐስ ኩባ አንድ ነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት እንደቅደም ተከተላቸው ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

አዲስ አበባ ሃምሌ 9/2009 /ኢዜአ/

አዘጋጇ ኬኒያ በአራት ወርቅ፣ በሰባት ብርና በአራት ነሐስ በድምሩ 15 ሜዳሊያዎች ወደ ካዝናዋ በማስገባት በአራተኝነት ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

ከ159 አገሮች የተውጣጡ ከሁለት ሺህ በላይ አትሌቶች በተሳተፉበት አስረኛው ዓለም አቀፍ ከ18 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በስድስት የውድድር ዓይነቶች 12 ወንዶችና 11 ሴቶች በድምሩ በ23 አትሌቶች ተወክላለች።

የልዑካን ቡድኑ ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።