ዜና ዜና

በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል---አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በአማራ ክልል በ2009 የበጀት ዓመት ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳደሩ ለክልል ምክር ቤቱ ባቀረቡት የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ሪፖርት እንደገለፁት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ርብርብ ተደርጓል።

በተለይም ባለፈው የክረምት ወቅት በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን ግርግር በህብረተሰቡ ተሳትፎ በማረጋጋት የህዝቡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል።

ከዚህ በተጓዳኝም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በማከናወን እየተመዘገበ ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ፍጥነቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ጥረት መደረጉን አቶ ገዱ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
በጥልቅ ተሀድሶው ወቅት የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን በመለየት ለመፍታት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መሰራቱም ጠቅሷል፡፡

የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ በተደረገው ጥረትም ካለፈው ዓመት ከሰባት ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ያለው 95 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብን አስታውቀዋል።
በመስኖ ከለማው መሬት ከ130 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ፣ ህብረተሰቡን በነቂስ በማሳተፍ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራና የጣና ሃይቅን ከእምቦጭ አረም በመከላከል የተሻለ ተግባራት መከናወኑም ገልጸዋል።

በገጠር የንፁህ መጠጥ ውሃን ለማዳረስም ከስምንት ሺህ 300 በላይ የውሃ ተቋማትን በመገንባት ከአንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

አዳዲስ የስራ እድል ለመፍጠር በተደረገው ጥረትም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ በመስጠትና የብድር ገንዘብ በማመቻቸት ከ610 ሺህ በላይ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆናቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡
የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋፋት በተጓዳኝ የጥራት ማስጠበቂያ ፓኬጆችን እንዲተገበሩ በማድረግ መሻሻሎች እንዳሉት ነው ያወሱት አቶ ገዱ፡፡

ባለሃብቶች ወደ አካባቢው መጥተው እንዲያለሙ በተከናወነው ስራም ከ36 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አንድ ሺህ 800 ፕሮጀክቶች ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና መንደሮችን በማስፋፋት የክልሉን ኢንዱስትሪ ህዳሴ ጉዞ ለማሳካተም ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ሆኖም የተመዘገቡ ውጤቶች የሚያበረታቱ ቢሆንም ከህዝቡ የልማት ፍላጎት አንፃር የሚከናወኑና በቀጣይ በልዩ ትኩረት የሚሰሩ ቀሪ ተግበራት እንዳሉም አቶ ገዱ አብራርተዋል።

በተለይም ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደርን ማስፈን ፣ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርን መግታት፣ ህገ ወጥ ንግድን መከላከል፣ የውጭ ንግድ ከማሳደግ አንፃርም የተቀዛቀና ከቀደሙት ዓመታት የቀነሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

የመንግስት ሰራተኛው ወደ ተቀራረበ አገልገሎት አሰጣጥ በማምጣትና የትራፊክ አደጋን በመቀነስም የእቅዱን ያህል ማከናወን እንዳልተቻለ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቀሱት፡፡

በቀጣይ እነዚህና ሌሎችንም ክፍቶች ለማስተካከል በትኩረት እንደሚሰራ ነው አቶ ገዱ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ያመላከቱት ፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት ምክር ቤት ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ውሎም ርዕስ መስተዳደሩ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ መወያየቱንና ከአባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ነገ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ትናንት ማምሻውን የተጀመረውና እስከ ሐምሌ 11/2009 ዓ.ም የሚቆየው የምክር ቤቱ ጉባኤ የጠቅላይ ፍርድ ቤትን እቅድ አፈፃፀም፣የኦዲት ሪፖርት፣የቀጣይ ዓመት በጀት እንደሚያጸድቅ ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡

እንዲሁም የተሻሻለውን የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ፣ልዩ ልዩ ሹመቶችና ስንብት እንደሚከናወንም ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ባህርዳር ሀምሌ8/2009(ኢዜአ)