ዜና ዜና

በጋምቤላ ክልል "ሚሞሳ" የተባለው መጤ አረም በሰብልና በግጦሽ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው

በጋምቤላ ክልል "ሚሞሳ" ተብሎ የሚጠራው መጤ አረም በሰብልና በግጦሽ ማሳቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ አርሶና ከፊል አርብቶደሮች ገለጹ።

የክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም በበኩሉ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት እየተስፋፋ ያለውና በአካባቢው አጠራር "እትንኩኝ" ተብሎ የሚጠራውን ይህን አረም ለመከላከል የምርምር ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ አርሶና ከፊል አርብቶአደሮች በሰጡት አስተያየት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከሰተው "አትንኩኝ" የተባለው መጤ አረም በእርሻና በግጦች መሬት ላይ በፍጥነት እየተዛመተ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በአቦቦ ወረዳ የመንደር 13 ነዋሪ አርሶአደር ኑርዬ አንሸቦ እንደገለጹት፣ አረሙ እሾሀማ ከመሆኑ በተጨማሪ ስርጭቱ ፈጣን በመሆኑ በሰብልና በግጦች መሬት ላይ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

"አትንኩኝ የተባለው መጤ አረም በሰብል ላይ በተለይ በሰሊጥ፣ በሩዝና ሌሎች ቁመት በሌላቸው ሰብሎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና የምርት መቀነስ ከፍተኛ ነው" ያሉት ደግሞ የዚሁ መንደር አርሶና ከፊል አርብቶአደር ታሪኩ በሊሁን ናቸው።

አረሙ ምርታማነታቸውን ከመቀነስ ባለፈ በከብቶቻቸው የግጦሽ መሬት ላይም ጭምር ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

አርሶና ከፊል አርብቶአደሮቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሚመለከተው አካል ችግሩ የሚቃለልበትን ሁኔታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል።

የክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ ኮንግ ጆክ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ተቋሙ መጤ አረሙ በክልሉ በሰብልና በግጦች መሬት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በዳሰሳ ጥናት በመለየት ለመፍትሄው የምርምራ ሥራዎችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት መጤ አረሙ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች  መሰራጨቱን ጠቁመው ፣በተለይም በአራት ወረዳዎች ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

ተቋሙ ባካሄዳቸው የምርምር ስራዎች አረሙን በሰው ጉልበት ከመከላከል ባለፈ ኬሚካሎችን በመጠቀም ማጥፋት እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች መገኘታቸውና በቅርብ ጊዜም ጥናቱ ተጠቃሎ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በተቋሙ የሰብል ዘርፍ ተመራማሪ አቶ ዘሪሁን በላቸው በበኩላቸው "ሚሞሳ" ወይም ''አትንኩኝ'' ተብሎ የሚጠራው መጤ አረም የሰብልና የግጦሽ መሬትን በመሸፈን ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

እሾሀማ ከመሆኑ በተጨማሪ ጉበት የሚመረዝ ሚሞሲን የተባለ ኬሚካል የያዘ አረም በመሆኑ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የአረሙ አንዱ እግር እስከ 12 ሺህ የሚደርስ ፍሬዎችን ስለሚይዝ በከፍተኛ ፍጥነት የመስፋፋት ባህሪ ያለው መሆኑን አቶ ዘሪሁን ገልጸዋል።

ሚሞሳ በሳይንሳዊ ስሙ ዲፕሎራቲካ ተብሎ የሚታወቀው አረም ከአሜሪካ በናይጀሪያ በኩል ወደ አፍሪካ እንደገባ ከጋምቤላ ግብርና ምርምር ተቋም የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጋምቤላ ሃምሌ 7/2009 /ኢዜአ/