ዜና ዜና

አርሶ አደሮች ወቅታዊ የአየር ፀባይ መረጃን እንዲያገኙ የሚያስችሉ ማዕከላት ተቋቋሙ፡፡

አርሶ አደሮች እለታዊ እና ወቅታዊ የአየር ፀባይ ሀኔታን በቀላሉ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ማዕከላት በአራት ክልሎች በሚገኙ 50 ወረዳዎች መቋቋማቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው በአማራ ክልል 15፣ በኦሮሚያ ክልል 15፣ በደቡብ ክልል 10 እንዲሁም በትግራይ ክልል 10 በአጠቃላይ 50 ማዕከላት መቋቋማቸውን ገልጿል።

ታዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጡ የመጎዳታቸው አንዱ መንስኤ፥ የአየር ፀባዩን ማዕከል ያደረገ የሰብል አመራረት አለመጠቀማቸው መሆኑን በኤጀንሲው የአየር ንብረት ለውጥ ማላመድ እና ማለዘብ ዳይሬክተር ዶክተር ወጋየሁ በቀለ ይናገራሉ።

አርሶ አደሮቹ ስለ አየር ንብረት እና ጠባይ ወቅታዊ መረጃ የሚያገኙበት ስርዓት አለመኖሩ፥ ወቅትን መሰረት ያደረገ የሰብል መመረት እንዳይኖር አድርጓል።

እስካሁን ባለው አሰራር የአየር ትንበያ መረጃ የሚሰጠው፥ የከተማ እና ከተማ ቀመስ አካባቢ ነዋሪን ባማከሉ የመገናኛ ዘዴዎች መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ አርሶ አደሩ በቀጥታ የአየር ትንበያ መረጃ የሚያገኝባቸው ማዕከላት መቋቋማቸውን ዶክተር ወጋየሁ ተናግረዋል።

በ50 የገበሬ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች የተቋቋሙት እነዚህ ማዕከላት፥ አርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ የአየር ንብረት መረጃዎችን እንዲያውቅ የሚረዱ ናቸው።

የማዕከላቱ መከፈት የአየር ትንበያ መረጃዎች ለአርሶ አደሩ በትክክል እንዲደርሱ ከማድረጋቸው ባሻገር፥ ለግብርናው ምርትና ምርታማነት የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው፥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የመረጃ እና ክላይማቶሎጂ ሃላፊው አቶ መለስ ለማ አብራርተዋል።

የመረጃ ጣቢያዎቹ ለአርሶ አደሮቹ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ተብለው የተከፋፈሉ ግልፅ መረጃዎችን ያቀርባሉ።

ይህ ደግሞ አርሶ አደሮቹ ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ ሰብሎችን ለመዝራት እና ለማምረት እጅጉን ጠቃሚ መረጃን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ተብሏል።

ጣቢያዎቹ ለእያንዳንዳቸው ከ25 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ በአጠቃላይ ከ 27 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ተደርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም በማዕከላቱ የሚወጡ መረጃዎችን ለአርሶ አደሩ ተንትነው የሚያቀርቡ የግብርና ባለሙያዎችን፥ ለማሰልጠን ዝግጅት መጠናቀቁን ኤጀንሲው አመላክቷል።

ኤጀንሲው ዘንድሮ በተቋቋሙት 50 ጣቢያዎች ሳይወሰን ሌሎች ተጨማሪ ማዕከላትን እንደሚያቋቁምም አረጋግጧል።

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)