ዜና ዜና

ተምች የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም ዘለቄታዊ መፍትሄዎችን እያጤነ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ገለፀ፡፡

ተምች የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቋቋም ዘለቄታዊ መፍትሄዎችን እያጤነ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የተከሰተው የተምች ወረርሽኝ በቆሎንና ሌሎች ሰብሎችን በማጥቃት በምርታማነት ላይ ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ሌሎች ሰብሎችን በማጥቃት በተለይም በኢትዮጵያ በበቆሎ ሰብል ላይ  በስፋት መታየቱና እያደረሰ ካለው ጉዳት አንፃር በቀጣይ አገራዊ ምርታማነት ላይ ችግር ሳይፈጥር አማራጭ ዘለቄታዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ እያጤነ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ገልጿል፡፡  

አሜሪካ መጤ የሆነውን  ተምች በዘላቂነት ለመከላከልም ተምቹን የሚቋቋሙ ዝርያዎች ከውጭ እስከማስገባት የሚደርስ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ም/ዳይሬክተር ዶክተር በላይ ሃብተ ሚካኤል  እንደገለጹት ተምቹም ሆነ ሌሎች የሰብል በሽታዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ምርምር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ለዚህም ሲባል  ከግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ከከፍተኛ ተቋማት፣ የክልል የምርምር ተቋማትና ከግብርና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የተውጣጣ አማካሪ ካውንስል መቋቋሙን ዶክተር በላይ ተናግረዋል፡፡

ችግሩ ከተከሰተባቸው የአፍሪካ አገራትም ችግሩን የተቋቋሙበትን መንገድ ልምድ መወሰዱን የገለጹት የምርምር ባለሙያው ዶ/ር በላይ፣ በቀጣይ ልምዶቹ ተቀምረው ተግባራዊ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

ከአገራቱ በተገኘው ልምድ ተምችን የሚቋቋም ዝርያ ማስገባት የመጨሻ አማራጭ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር በላይ  ፣አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ  የፖሊሲ ለውጥ እስከመጠየቅ ሊደርስ ይችላል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ሀምሌ፣6/2009(ኢ.ቢ.ሲ)