ዜና ዜና

የትግራይና የሱዳን ገዳሪፍ ምክር ቤቶች ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቅንጅት እንደሚሰሩ ገለጹ፡፡

የትግራይ ክልልና  የሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ምክር ቤቶች ግንኙነታቸውን  ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን  ለማጠናከር  በቅንጅት እንደሚሰሩ ገለጹ፡፡

የሱዳን ገዳሪፍ ምክር ቤት የልኡካን ቡድን አባላት ከትግራይ ክልል አቻቸው ጋር የተሞክሮ ልምድ ልውውጥ አካሄደዋል፡፡

በመቀሌ ከተማ በተካሄደው በዚሁ ስነስርዓት ወቅት የትግራይ ምክር ቤት  አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ የክልሉ ምክር ቤት  ህገ መንግስቱ  በሰጠው ስልጣን መሰረት በህዝብ ድምፅ የተወከሉ 152 የምክር ቤት አባላት እንዳሉት ለልኡካን ቡድኑ ገልጸዋል።

የክልሉ ምክር ቤት በወረዳና ቀበሌ ደረጃም የህዝብ ውክልና ያላቸው ምክር ቤቶች እንዳሉት ያመለከቱት አፈ ጉባኤዋ በተዋረድ ባሉት ምክር ቤቶች የሴቶች ውክልና  50 ከመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

ህግ በማውጣት፤በጀት፣ አዋጆች፣ ደንቦችን በማፅደቅ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የፈፃሚውን አካል ስራዎች የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት እንዳለበት ነው ያስታወቁት።

የትግራይና የሱዳን ገዳሪፍ ምክር ቤቶች በህዝቦቻቸው መካከል ረጅም ዘመናት ያስቆጠ  የወንድማማችነት ግንኙነት አላቸው፡፡

ይህን ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር እየተባባሰ የመጣውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና ፀጥታ ማስከበርን ጨምሮ ሌሎችንም የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማጠናከር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ወይዘሮ ቅዱሳን አመልክተዋል፡፡

የገዳሪፍ  ምክር ቤት አባልና የልዑካን ቡድኑ አስተባባሪ ሚስተር መሓመድ ጠይብ አለበሽር በበኩላቸው "ከትግራይ ክልል ምክር ቤት የተጠያቂነት አሰራርን በመልካም ተሞክሮ ወስደናል" ብለዋል።

እንዲሁም ክልሉ ያስመዘገበው እድገት በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶችና ፈፃሚዎች ተቀናጅተው በመስራት  የተገኘ ውጤት እንደሆነ መገንዘብ እንደቻሉም ገልጸዋል።

ከክልሉ ያገኙትን መልካም ተሞክሮ ወደ ግዛታቸው ወስደው ተግባራዊ እንደሚያደርጉት የተናገሩት ደግሞ የገዳሪፍ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሚስተር ዓብደላ ራሕመተላ ናቸው፡፡

የትግራይ ምክር ቤት የተከተለው ነፃና ግልፅ አሰራር ክልሉ አሁን የደረሰበት  እድገት  ደረጃ ምስክር  መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ያገኙትን ልምድና ተሞክሮዎችን ከምክር ቤታቸው አሰራር ጋር  አጣጥመው ለመጠቀም ግብኣት እንደሚሆናቸው ነው ሚስተር ዓብደላ የተናገሩት፡፡

ግንኙነታቸውን  አጠናክረው በተለይም  ወጣቶች በህገወጥ አስኮብላዮች እየደረሰባቸው ያለውን ስቃይና እንግልት ለማስወገድ ተባብረው በቅንጅት ለመስራት ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ  አባላት በክልሉ መንግስትና ህዝብ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን፣ የሰማዕታት ሃውልትና  ታሪካዊው የአልነጃሺ መስጊድን ተመልክተዋል፡፡

 

  መቀሌ ሀምሌ 5/2009(ኢዜአ)