ዜና ዜና

"በ21 ኛዉ ክፍለ ዘመን ትልቁ የጦር ሰራዊት ሰላማዊ ዲፕሎማሲ ነዉ" ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር

በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. የኢፌዴሪ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በጽህፈት ቤታቸዉ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "በ21 ኛዉ ክፍለ ዘመን ትልቁ የጦር ሰራዊት ሰላማዊ ዲፕሎማሲ ነዉ" መሆኑን አስታወቁ፡፡

ኃላፊ ሚኒስትሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴን ግድብ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው በሰጡት ምላሽም ግብጽና ኡጋንዳ አብሮ መስራታቸዉ እኛን የሚያስደነግጥ ጉዳይ አይደለም ዳሩ ግን የራሳችንን ደህንነት ለመከላከል፤ ብሎም ግድቡ የሁሉም ዜጋ ላብ እንደመሆኑ ሀብታችንን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያ የማንንም ድጋፍ እንደማትፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በኡጋንዳ ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለዉን ጠንካራ ትስስር የሚያሣይ ነዉ ያሉት ሚኒስትሩ ብዙ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማዳበሪያ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ቁርኝት ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አክለውም ዶ/ር ነገሪ የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ሀገራቸዉን እንዲጎበኙ ለኢትዮጵያዊዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ አድርገዋል፤ ይህም ለሁለቱ ሀገራት ግጭት ሳይሆን ንግግር መፍትሄ መሆኑን በመረዳት መንገድ እየከፈቱ ለመሆኑ ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡

ከጋዜጠኞች ከተነሱላቸው ጥያቄዎች ደግሞ ምላሽ ሲሰጡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተለምዶ ቆሼ በሚባለው ስፍራ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን በደረሰዉ አደጋ መንግስት እና ህዝብ የተሰማቸዉን ሀዘን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ አክለዉም ከፈረንሳይ መንግስት ጋር በመተባበር አካባቢዉን ወደ ፓርክነት ለመቀየር ሀሳብ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

በህዳሴዉ ግድብ ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ አካላት የነበሩ መሆኑም በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን፣ እነዚህም አካላት ዓላማቸዉ በሀገሪቱ ላይ ሰላም እንደሌለ ለማስመሰል አስበው ያቀዱት ነው በማለት እንደ ሀገር ግን አንዳችም ስጋት የሚጥል አደጋ ፈጽሞ አለመኖሩን አስምረውበታል፡፡

ባልተረጋገጠ መረጃ መንግስት አቋም አይወስድም ያሉት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር የመከላከያ ኃይላችን በታሪክ፣ በእሴት፣ በቴክኖሎጂም ይሁን በሰዉ ኃይል አቅም አሁን የደረሰበት ደረጃ የተጠናከረ እንደመሆኑ ከየትኛዉም ወገን የሚሰነዘርበት ጥቃት አስጊ አይሆንም ብለዋል፡፡

ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መምጣት የሚፈልጉትም ኃይላት ህገ-መንግስቱን አክብረው ወደ አደባባይ የሚመጡ ከሆነ የተመቻቸዉ መንገድ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉ ይቀጥላል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጽዳትን በተመለከተ በከተማው ውስጥ የሚታየውን የጽዳት ጉድለት ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያስችል ዘንድ በአዲስ አበባ እየተዋወቀ ያለዉ አዲሱ ማስተር ፕላን እነዚህን ችግሮች ከግምት ውስጥ ያከተተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ማስተር ፕላኑ አዲስ አበባን አረንጓዴ ለማድረግ ብሎም ለተፈጥሮ ልማት ትርጉም ያለው ትኩረት እንዲሰጠው ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በቅርቡም መስተዳድሩ ስራ ላይ ሲያውለው ችግሮች በዘላቂነት የሚቀረፉበትን እድል እንደሚያሰፋ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሰሞኑን ብዛት ያላቸዉ መሪዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ልማታችንን የሚደግፉ ሀገራት አጋርነታቸዉን ለማሳየት የሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊ ስልት መሆኑን ያመለከቱት ዶ/ር ነገሪ በሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት አለመሻከር ለሀገራቱ ግንኙነት መዳበር አንዱ መንገድ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

መጋቢት 10/2009