ዜና ዜና

ለታላቁ ህዳሴ ለግድቡ ያደረግነው ሙያዊ ድጋፍ ወደ ተግባር ተቀይሮ ማየታችን አስደስቶናል- የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሰራተኞች

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያደረጉት ሙያዊና የገንዘብ ድጋፍ ወደ ተግባር ተቀይሮ በማየታቸው መደሰታቸውን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ሠራተኞች ገለጹ።

ሠራተኞቹ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ጎብኝተዋል።

በሶስተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉብኝት የተሳተፉ የተቋሙ ሠራተኞች ስለግድቡ ቀድሞ ካዩትና ከሰሙት ባሻገር ያለበትን ደረጃ በአካል ተገኝተው በማየታቸው መደሰታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ እንደገለጹት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የሙያና የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ግንባታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የመሬትና አለት ጥናትም አከናውነዋል። ይህ ደግሞ በተግባር ተተርጉሞ ማየታቸው አስደስቷቸዋል።

የኢንስቲትዩቱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ መርሻ ግድቡን ለሁለተኛ ጊዜ መጎብኘታቸውን አመልክተው፤ ቀድሞ ካዩት በጣም ብዙ ለውጥ ያለው መሆኑንም ገልፀዋል።

የግደቡን ግንባታ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት ወይዘሮ መሰረት አርጋው፣ ክብነሽ ወልደሚካኤልና መልካምነሽ አደፍርስ ከሰሙት ይልቅ ባዩት ነገር ደስተኞች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የተቋሙ ሰራተኞች በሁለት ዙር   የሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውንና የ10 ሺ ብር የሎተሪ ትኬትና የግድቡን ቲሸርቶች በመግዛት የግድቡ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

ተቋሙ ግድቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ የመሬትና አለት ጥናት ሲያከናውን ስለመቆየቱ የተቋሙ ባለሙያ ኢንጂነር አብርሃም ሙሉነህና አቶ ግርማ አሰሙ ምስክሮች ናቸው።

ሰራተኞቹ በግድቡ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው አማካኝነት ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ የግድቡን ግንባታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ሲያደርጉት የነበረውን  ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት 3 ሺ 750 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩት 10 የኃይል ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።

ከዋናው ግድብ በስተ ምስራቅ ያለው የሳድል ግድብ ግንባታም የመጨረሻ የአርማታ ሙሊት ስራ እየተሰራ ነው።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 58 በመቶው መጠናቀቁ ተገልጿል።

አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2009(ኢዜአ)