ዜና ዜና

''ልዩ ጥቅሙ የተዛባን ታሪክ ለማስተካከልና አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመገንባት በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር የሚያደርግ ነው'' ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ- የኢፌዲሪ የመንግስት ኮ/ጉ/ፅ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር

የኢፌዲሪ የመንግስት ኮ/ጉ/ፅ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል::

በማብራሪያቸው ከዳሰሱት ጉዳዮች አንዱ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅም አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ መሰረት ያደረገ ነው::

ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንደተናገሩት ይህ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመመራቱ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለእይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴ ከማስተላለፉ በፊት በኢህአዴግ ም/ቤት፣ በኦሮሚያ ክልል መሪ ፓርቲ /ኦህዴድ/፣ በኦሮሚያ ብ/ክ/መ/አስተዳድር፣ በፌደራል ተቋማት ሀላፊዎች እና በህግ ተቋማት ዘንድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል::

ረቂቅ አዋጁ በቀጣይም በህዝቦች ዘንድ ውይይት እንደሚደረግበት የተናገሩት ዶ/ር ነገሪ ልዩ ጥቅሙ የተዛባን ታሪክ ለማስተካከልና አዲሲቷን ኢትዮጵያ በመገንባት በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል::

ልዩ ጥቅሙ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ የኦሮሚያ ብ/ክ/መንግስት መ/ቤቶች ተቀጥረው የሚሰሩ ሌሎች ብሄሮችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል::

አዋጁ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ የመስፋፋት ዕድል እንዲኖራት አያደርግም ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሚኒስትሩ መልስ ሲሰጡ የወሰን ማካለል ስራ ራሱን ችሎ የሚሰራ በመሆኑ በዚህ በኩል ምንም ስጋት የሚፈጠርበት ሁኔታ አይኖርም ብለዋል::

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ልዩ ጥቅም በህገ መንግስቱ እንዲሰፍር ያደረጉት የኦሮሞ ህዝብን ጨምሮ መላው የሀገራችን ህዝቦች ናቸው ስለዚህ ጥቅሙ የኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ነው ብለዋል ሚኒስትሩ::

ሰኔ 24/2009