ዜና ዜና

አገር በቀል የሰላም ፍልስፍናዎች በሳይንሳዊ መንገድ ተደግፈው ሚናቸውን እንዲጫወቱ እየተሰራ ነው

በህብረተሰቡ ውስጥ የሰላምን እሴት የሚሰብኩ አገር በቀል ፍልስፍናዎች በሳይንሳዊ መንገድ ተደግፈው ሚናቸውን እንዲጫወቱ እየሰራ መሆኑን የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ገለጸ፡፡

ዩኒቨርስቲው ከህንድ ጂያን ማህበረሰብ ጋር በመተባበር " አገር በቀል የሰላም ፍልስፍናዎችን ለሰላም ግንባታ ያላቸው ፋይዳ " በሚል ሃሳብ ያዘጋጀው አለም አቀፍ ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው።

የአንዲት ሃገር የሰላም ግንባታ ቀጣይነት እንዲኖረው በማህበረሰብ ሰላም ላይ የሚያተኩሩ ፍልስፍዎችን በሳይንሳዊ መንገድ ማሳደግ እንደሚገባ በዩኒቨርስቲው የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ቢንያም መኮንን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት የማንነት መገለጫ የሆኑ አገር በቀል ፍልስፍናዎች በአለም አቀፍ ደረጃ የሰላም ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ እያስተዋወቀ ነው፡፡

በሳይንሳዊ መንገድ ተደግፈው ሚናቸውን እንዲጫወቱና ቀጣይነት እንዲኖራቸውም ዩኒቨርስቲው እየሰራ ነው፡፡

በዩኒቨርስቲው የፍልስፍና መምህር እያሱ በርንቶ " የአፍሪካውያን ፍልስፍናዎች ለአፍሪካውያን የሰላም ግንባታ ያላቸው ሚና" በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንዳሉት፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን ፍልስፍና በአህጉሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና በሌላው አለም ፍልስፍና ውስጥ ተፅዕኖ ስራ እንዳይወድቁ ያግዛል።

አገር በቀል ፍልስፍናዎችን በማሳደግ ማንነትን የሚጎዱ ባዕድ ፍልስፍናዎችን ለመከላከል ያላቸው ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም ነው መምህር እያሱ ያመለከቱት።

ከህንድ የመጡ ፕሮፌሰር ራጅማል ጃይን በበኩላቸው ፣በአለም አቀፍ ደረጃ ሰላም እንዲሰፍን በአገር በቀል የሰላም ፍልስፍናዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በህንድ የጃይን ፍልስፍና በአፍሪካ ደረጃ በማስተዋወቅ ለዓለም ሰላም ግንባታ የራሱን አስተዋፅኦ እንዲኖረው ለማስቻል ኮንፈረንሱ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

"የአፍሪካና የጂያን ፍልስፍናዎች ጎልተው እንዲወጡ በማድረግ በዓለም አቀፍ የሰላም ግንባታ ላይ አስተዋዕኦ እንዲያደርጉ ይሰራል "ብለዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ክንዳያ ገብረህይወት " ኮንፈረንሱ በሰላም ላይ የሚያጠነጥኑ ፍልስፍናዎች በዓለም ደረጃ ለማስተዋወቅ ትልቅ ትርጉም አለው "ብለዋል።

ወጣት ምሁራን ለአገር በቀል ፍልስፍናዎች ትኩረት እንዲሰጡ ኮንፍረንሱ እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ትናንት በተጀመረው ኮንፍረስ ከኢትዮጵያ ሌላ ከህንድ ፣ከኬንያና ከኢስያ ሃገራት የመጡ ከ70 በላይ ምሁራንና ተማሪዎች እየተሳተፉ ነው።

መቐለ ግንቦት 11/2009/ኢዜአ/