ዜና ዜና

የሳውዲ ተመላሾች በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ እየተሰራ ነው

የሳውዲ ተመላሾች ወደ ሃገራቸው ከገቡ በኋላ ያለ እንግልት ወደ ቤተሰቦቻቸው በሰላም እንዲቀላቀሉ እየሰራ መሆኑን የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ግርማ ሸለመ እንደገለፁት ተቋማቸው በሳውዲ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎችን ወደ ሃገር ለመመለስ ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ጋር በአባልነት እየሰራ ነው፡፡

ችግሩ በአጋጣሚ የተከሰተና መንግስትም ሆነ ዜጎች ያልተዘጋጁበት በመሆኑ የሚፈጠረውን የስነልቦናና የኢኮኖሚ ጫና ለመፍታት ክልሎች ለተመላሾቹ ድጋፍ የሚያደርጉበትና ወደ ስራ የሚያስገቡበት ሁኔታ ላይ የተቋሙ የበላይ አመራሮች ከክልሎች ጋር ምክክር አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

"ዜጎች በአሁን ሰአት በብዛት እየተመለሱ አይደለም" ያሉት አቶ ግርማ የጊዜ ገደቡ ማብቂያ ላይ ብዙ ዜጎች ይመለሳሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ ተቋሙ የቀውስ ጊዜ እቅድ በማዘጋጀት በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ተቋሙ ዜጎች ወደሃገር ከተመለሱ በኋላ በቀጣይነት መከናወን ስላለበት ተግባርም ውይይት ተደርጎበታል ፣የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም እየተከናወኑ ነው ብለዋል ፡፡

ከስደት ተመላሾቹ ሀገራቸው እንደደረሱ ለዚህ ጉዳይ ተብሎ በተቋቋመና 17 አባላት ባሉት ግብረ ሃይል ሙሉ አድራሻቸውን በመመዝገብ የተደራጀ መረጃ እየተያዘ መሆኑንም ገልፀው ይህም በቀጣይ ለሚደረጉ የማደራጀትና ወደስራ የማስገባት ሄደቱን እንደሚያቀላጥፈው ጠቁመዋል ፡፡

ዜጎችን በሰላም ወደ ሃገራቸው ለመመለስ 40 ቀናት ብቻ ቀርቷቸዋል ያሉት አቶ ግርማ ያፈሩትን ገንዘብና ንብረት እንዲሁም ከምንም በላይ ህይወታቸውን ይዘው ወደ ሃገራቸው በሰላም እንዲገቡ መንግስት ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል፡፡

ይህም ጥረት በመንግስት ብቻ ሳይሆን በቤተሰብና በጓደኛ መታገዝ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ሀገር ውስጥ ያለ ቤተሰብ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በስልክ፣ በኢሜልም ይሁን በማህበራዊ ሚዲያዎች ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ዜጎቹ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ ግፊቱ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

"የሳውዲ መንግስት ምህረት ያደርጋል አይጨክንም፤ የጊዜ ገደቡ እስኪያልቅ ስሩ" እያሉ የሚያዘናጉትን ህገወጥ ደላሎች ዜጎች መስማት እንደሌለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ሀገራችን የሌላ ሃገር ዜጋን በመቀበል ያተረፈችውን ስም በራሷም ዜጎች አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ገልፀው ከስደት ተመላሾችን "እንኳን ደህና መጣችሁ "ብሎ መቀበል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ግንቦት 11/2009/ኢዜአ/