ዜና ዜና

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ድርቅና ሁከቶችን ተቋቁማ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ በዓለም ተጠቃሽ አገር መሆን መቻሏን የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ሰኔ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ለተባበሩት መንግሥታት የማኅበራዊና ፋይናንስ ካውንስል የሚያቀርበውን "የ2017 የዘላቂ ልማት ግቦች የፈቃደኝነት ብሔራዊ ግምገማ" ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ አስገምግሟል።

ድህነትና ረሃብን  ማጥፋት፣ ጤናማ ሕይወት መምራት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታና ኢንዱስትሪ ፈጠራ፣ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲሁም የውሃ ሥነ-ምህዳርን በዘላቂነት መጠበቅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚገመገሙ የዘላቂ ልማት ግቦች ናቸው።

እነዚህ ዘላቂ የልማት ግቦች ከሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር ተመጋጋቢ ናቸው።

ክምክር ቤቱ አባላት የእቅዱ ዘመን አፈጻጸም ያለበት ደረጃ እንዲቀርብ ጥያቄ ቀርቦ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ይናገር ደሴ እንደገለጹት፤ አገሪቷ በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅና ሁከቶች እንዲሁም የዓለም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ሳይበግራት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሁለት ዓመታት ውስጥ ፈጣን እድገት አስመዝግባለች ነው ያሉት።

በ2008 በጀት ዓመት የአገሪቷን ኢኮኖሚ በ11 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዞ ስምንት በመቶ ያደገ ቢሆንም ከዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረው ፈተና አኳያ የተመዘገበው ፈጣን እድገት ነው።

"በዚህም በዓለም ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ አገሮች መካከል አንዷ መሆኗን አስመስክራለች" ብለዋል።

በ 2008 ዓ.ም የሸቀጦችና የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበር ጠቁመዋል።

በወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራዎች፣  የሥርዓተ ፆታ፣ የሰው ኃብት ልማት፣ ፍትሃዊ የኃብት አጠቃቀም ያሉበት ደረጃ በሪፖርቱ ላይ በዝርዝር እንዲቀርቡም ምክር ቤቱ ጠይቋል።

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2009 (ኢዜአ)