ዜና ዜና

የኢትዮ - ኬኒያ የአንድ ማዕከል የድንበር ፍተሻ ከሁለት ወር በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል

ኢትዮጵያ ከኬኒያ ጋር ስምምነት ላይ የደረሰችበት የአንድ ማዕከል የድንበር ላይ ፍተሻ ከሁለት ወር በኋላ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

ኢትዮጵያን በተለያዩ የልማት ኮሪደሮች ከጎረቤት ሃገራት ጋር የሚያገናኙ የመንገድ ግንባታዎች ተከናውነዋል፤ በግንባታ ላይ የሚገኙም አሉ።

ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆነውና በሞጆ - ሀዋሳ ሞያሌን አቋርጦ ኬኒያ የሚገባው መንገድ ግንባታ፥ አፍሪካን በመሰረተ ልማት ለማገናኘት የተያዘው እቅድ አካል እንደመሆኑ ኢትዮጵያን በኬኒያ በኩል ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚያገናኝ ነው።

በዚህ መስመር ድንበር ተሻግሮ ለመውጣትም ሆነ ለመግባት የሚፈልግ ሰውም ሆነ የሚያንቀሳቅሰው ንብረት ፍተሻ ይደረግለታል።

አሁን ላይ ባለው አሰራር ፍተሻው በሁለቱም ሀገራት ድንበር ላይ የሚደረግ እንደመሆኑ፥ የእንቅስቃሴው ቁጥር በጨመረ ቁጥር ለአሰራር ምቹ ሁኔታን አይፈጥርም።

ይህን ታሳቢ ያደረገና የአንድ ማዕከል የድንበር ላይ ፍተሻ ሂደት እንዲኖር ኢትዮጵያና ኬንያ የዛሬ ሶስት አመት ከስምምነት ደርሰው ነበር።

ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተጀመረው ማዕከል ግንባታ፥ በኬኒያ በኩል ያለው ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ደግሞ 98 በመቶ ደርሷል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ፥ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ማዕከል ከሜጋ ሞያሌ መንገድ ፕሮጀክት ጋር በአንድ ላይ እየተከናወነ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ማዕከሉ ስራ ሲጀምር በመስመሩ የሚንቀሳቀስ ሰውም ሆነ ንብረት አንድ ጊዜ ብቻ ይፈተሻል፤ ከኢትዮጵያ የሚወጣው ኬኒያ ላይ ሲፈተሽ ከኬኒያ የሚወጣው ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ባለው ማዕከል ፍተሻ ይደረግለታል።

በየማዕከላቱ የሚመለከታቸው የፍተሻ አካላት፤ የገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን፣ የኢሚግሬሽንና የመሳሰሉት ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በሁለቱም ሀገራት ማዕከል ላይ እንዲገኙ ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለስልጣን የፍተሻ ቡድኑን በበላይነት ይመራዋል፤ በባለስልጣኑ የትራንዚት ፕሮግራም አሰራርና ልማት ቡድን አስተባባሪ አቶ ሀይሌ ገብረእግዚህአብሄር የአሰራር ሰነዶችን ሃገራቱ በጋራ እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ሲሚንቶ፣ በቆሎና ሌሎች ምርቶች በኬኒያ ሲወጡ፥ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ደግሞ በመስመሩ ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ።

የትራንዚት ፕሮግራም አሰራርና ልማት ቡድን አስተባባሪው ማዕከሉ መገንባቱ ቀልጣፋ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን በበኩሉ፥ የአንድ ማዕከል የፍተሻ አገልግሎት መኖር የሎጅስቲክ ስርዓትን ለማቀላጠፍ ለተያዘው ግብ ትልቅ አቅምን ይፈጥራል ብሏል።

ይህ ማዕከል እንደሙከራ ታይቶም በሌሎች የሃገሪቱ የልማት ኮሪደሮች ላይ ለመተግበር ጥናት ይደደረጋል ተብሏል።

በባለስልጣኑ የሎጅስቲክ ማስተባበሪያና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ይሁኔ፥ የአንድ ማዕከል የፍተሻ አገልግሎቱን በጅቡቲ በኩል ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ካለው መሰረተ ልማት አኳያ ግን ይህ የአንድ ማዕከል የፍተሻ አገልግሎት በኬኒያ በኩል መገንባቱንም ጠቁመዋል።

ግንቦት 10፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)