ዜና ዜና

የፍርድ ቤቶች የአሰራር ስርዓት መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

የዳኞችን የአሰራርና የቀጠሮ አሰጣጥ ሰርዓት ጨምሮ ሌሎች አሰራሮችን የሚመለከት መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ገለፀ።

ኢትዮጵያ ከሕገ መንግስቱ እና እሱን መነሻ አድርገው ከወጡ ሕጎች በስተቀር፥ አሰራሩ የሚመራበት የፍርድ ቤቶች መተዳደሪያ ሰነድ የላትም።

ብዙ የዓለም ሀገራት ግን የፍርድ ቤት አሰራር ሰርዓታቸውን ከቀጠሮ አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ዳኞች ቁጥጥር ሰርዓት ድርስ የሚመሩበት ሰነድ አላቸው።

ይህ ሰነድ በኢትዮጵያ ስለሌለ ቀጠሮ የሚሰጠው እንደየ ጉዳዮቹ እና ዳኞቹ ሁኔታ በወጣ ገባነት ሲሆን፥ ዜጎች ከወራት እስከ ሰባት ዓመት በቀጠሮ ሲመላለሱ ይስተዋላል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ፀጋዬ አስማማው እንደተናገሩት፥ እንዲህ ያለው ችግር በተለይ በሰበር ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስፋት ይታያል።

በቃሊቲና ሌሎች ማረሚያ ቤቶች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዙ ታራሚዎች፥ በፍርድ ቤቶቹ የቀጠሮ መራዘምና በአፋጣኝ ውሳኔ አለማገኘት ችግርን በተደጋጋሚ በቅሬታ ያነሳሉ፡፡

በዚህ መልኩ የሚስተዋል የቀጠሮ መንዛዛት ችግር መኖሩን የሚናገሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አጣሪ ዳኛ ወይዘሮ ዘውዲቱ ታደሰ፥ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚቀርቡ ባለጉዳዮች ከሚደርስበቸው መጉላላት ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚጋለጡ ያረጋግጣሉ።

የዳኞች ቁጥር ከጉዳዮች ጋር አለመመጣጠንን ጨምሮ በሀገሪቱ ሕገ መንግስት መሰረት የመጨረሻ ወሳኔ የጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሆኑ ከመላው ሀገሪቱ በርካታ ጉዳዮች ወደ ዚህ ፍርድ ቤት እንዲመጡ መገደዳቸው ለቀጠሮ መንዛዛት ተጠቃሽ መንስኤ ናቸው።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዚህ መልኩ ለዘመናት የተሻገረ የፍርድ ቤቶች የቀጠሮ መንዛዛት ችግርን ለማስቀረት፥የፍርድ ቤቶች አሰራርን የሚመለከት ሰነድ (ጁዲሻል ፓሊሲ) እያዘጋጀ ነው።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋዬ አስማማው፥ ሰነዱ በፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት እና በስርዓት ለመምራት ያለመ ነው ብለዋል።

የፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቄራንዮ ምድብ ዳኛና አስተባባሪ ዘነበ ገብረ እንደሚሉት፥ የአሰራር ሰርዓቱ መዘጋጀቱ በዳኝነተ አካሉ የሚሰጡ ረጃጅም ቀጠሮዎችን በማስቀረት ተጠያቂነትን ለመዝርጋት ያስችላል።

ባሳለፍነው ወር የተጀመረው የሰነድ ዝግጅቱ በቀጣይ ዓመት ተጠናቆ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን፥ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰነዱ ወደ ስራ እስኪገባ ድረስ ፍርድ ቤቶችን በመፈተሽ ረጃጅም ቀጠሮዎች እንዲታጠፉ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው

አጫጭር ቀጠሮዎች እንዲሰጡ የሚያስችሉ አስተዳዳራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ፀጋዬ ተናግረዋል።

በእስካሁኑ አስተዳዳራዊ እርምጃ ለውጥ መምጣቱን የተናገሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፥ መመሪያው ተግባራዊ ሲደረግ የፍርድ ቤቶች አሰራር የተቀላጠፈ እና የተንዛዙ ቀጠሮዎችም የሚቀንሱበት እድል ይፈጠራል ብለዋል።

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ)