ዜና ዜና

በኢሉአባቦር ዞን የተከሰተው ተምች በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ ነው

በኢሉአባቦር ዞን 13 ወረዳዎች የተከሰተው ተምች በመስኖ በለማ ሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመቆጣጠር በዘመቻ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ እንደገለጹት ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በዞኑ የተከሰተውን " ፎል አርሚ ዎርም" የተባለውን ተምች በባህላዊ ዘዴና ጸረ -ተባይ መድኃኒት በመርጨት ለመቆጣጠር እየተሰራ ነው፡፡

አርሶአደሮች ሁሉንም ቀበሌዎች ከተምቹ ለመከላከል ተደራጅተው በባህላዊ መንገድ ማሳቸውን እያጸዱ ሲሆን በተጨማሪ ተምቹ በታየባቸው ማሳዎች ላይ ከ5 ሺህ ኪሎግራም በላይ ጸረ -ተባይ ርጭት ተካሂዷል፡፡

እስከ አሁን ድረስ በተካሄደው የመከላከል ስራም ተምቹ ከታየበት 4 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ ከ3ሺ ሄክታር በላይ ማጽዳት ተችሏል፡፡

ተምቹ የሚራባውና የሚንቀሳቀሰው ሌሊት ሌሊት ነው" ያሉት ምክትል ኃላፊው ይህም በአጭር ጊዜ ለማጥፋት አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ተምቹ በዞኑ ሁሉም ቀበሌዎች ተስፋፍቶ በመጪው የመኸር ወቅት የሚለማውን ሰብል እንዳይጎዳም ለማጥፋት ዘመቻው ከ50ሺህ በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ከመቱ ወረዳ ቦቶ ቀበሌ አርሶአደሮች መካከል አቶ ሀብታሙ ዲላላ በሰጡት አስተያየት "በአንድ ለአምስት አደረጃጀት በመታቀፍ ተምቹን ከማሳ ውስጥ የመልቀም እና የማስወገድ ስራ እያከናወንን እንገኛለን "ብለዋል ።

ተምቹን በማሳ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩ ሰብል ያጠፋል ብለው ሰግተው እንደነበር ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት እያካሄዱ ባለው የዘመቻ ስራ ከማሳቸው ለማስወገድ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

"በባለሙያዎች በተሰጠን ትምህርት መሰረት ለአንድ ሄክታር መሬት ሁለት ሊትር ጸረ ተባይ መድኃኒት ቀርቦልን ተምቹ በታየባቸው ማሳዎች ላይ እየረጨን ነው"ብለዋል፡፡

ተምቹን በባህላዊ ዘዴና ጸረ ተባይ መድኃኒት በመርጨት መከላከል ከጀመሩ ወዲህ የበቆሎ ሰብላቸው መልሶ ማቆጥቆጥ እንደጀመረም አርሶአደሮቹ ተናግረዋል፡፡

ናስሮ አባድር የተባሉት አርሶ አደር በበኩላቸው ተምቹን በማሳቸው እንዳዩ ለልማት ጣቢያ ሰራተኞች በማሳወቅ ጸረ ተባይ መድኃኒት ቀርቦላቸው በመርጨት እየተከላከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

መቱ ግንቦት 9/2009/ኢዜአ/