ዜና ዜና

ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለጹ

የአካባቢያቸውን ልማት ከማጠናከሩ በተጓዳኝ ክራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ሰባተኛው የፍትህ ሣምንት በድሬደዋ አስተዳደር ትናንት በተከበረበት ወቅት ተሳታፊ ነዋሪዎች እንደገለጹት ከፍትህ አካላት ጋር ተቀናጅተው የአካባቢያቸውን ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ተግባራትን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የሀገር ሽማግሌው አቶ ዜና በየነ በሰጡት አስተያየት "የህግ የበላይነት መስፈን ለሰላም፣ለልማትና ለሀገር ዘላቂ እድገት መሠረታዊ በመሆኑ የፍትህ አካላት ለዚህ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል" ብለዋል፡፡

ቤተሰብ ፣ማህበረሰብና የፍትህ አካላት እርስ በርስ ከተባበሩና ለአንድ ተልዕኮ ከተንቀሳቀሱ አፍራሽ ድርጊቶች ቦታ እንደማይኖራቸው የተናገሩት ደግሞ አባገዳ አብዱልማክ ዩኒስ ናቸው፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የኃይማኖት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው በበኩላቸው "በየደረጃው በሚገኙ የፍትህ ተቋማትም ሆነ በዘርፍ መስሪያ ቤቶች ለተነሱ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባል "ብለዋል፡፡

በጥልቅ ተሃድሶ ላይ ለህዝብ ቃል የተገቡ ጉዳዮች በቃል መቅረት እንደሌለባቸው ጠቁመው ሆኖም በፍርድ ቤቶች አካባቢ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻሎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

አቶ አብዱልአዚዝ ያሲን የተባሉ ነዋሪ እንዳሉት በየዓመት የፍትህ ሣምንትን ጠብቆ ከህብረተሰቡ ጋር መወያየት ብቻ ሣይሆን በየቀበሌው መድረኮች በመፍጠር ህዝቡ ልማቱና ሠላምን እንዲጠበቅ መደገፍ ተገቢ ነው፡፡

" ወጣቱ ሰላምና ልማትን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፤ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን የኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ " ያለው ደግሞ ወጣት ሱሌይማን አሊ ነው፡፡

የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ከማጠናከሩ ጎን ለጎን ክራይ ሰብሳቢነትንና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አብደላ አህመድ "በሀገሪቱ እየተመዘገቡ የሚገኘው ፈጣን ልማት ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የፍትህ አካላት ለህግ የበላይነት መከበር ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል "ብለዋል፡፡

የፍትህ አካላትና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት አቶ በላቸው አቺሶ በአንዳንድ የፍትህ አካላት ዘንድ የሚስተዋሉ የሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለማጥራት የተጀመሩ ሥራዎች ስኬታማ የሚሆኑት ህብረተሰቡ የራስን ኃላፊነት ሲወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፍትህ ሣምንት በዓሉ በድሬደዋ የተከበረው በህዝባዊ ውይይት ፣ በፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ፣ በተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድሮች ሲሆን የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የአስተዳደሩ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

ግንቦት 9/2009 /ኢዜአ/