ዜና ዜና

በዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ

በዱባይ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታወቁ።

ኢትዮጵያዊያኑና ትውልደ ኢትዮጵያዊኑ ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ የሎተሪ ድጋፍ የሚውል አንድ ራቫ ፎር ተሽከርካሪ በስጦታ አበርክተዋል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤትም የተሽከርካሪ ቁልፍ ተረክቧል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እንደቀጠለ መሆኑ ይታወቃል።

በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በገንዘብ፣ በእውቀትና ቦንድ በመግዛት የሚያደርጉት ድጋፍ የግድቡን ግንባታ ከመጨረሻው እስኪደርስ እንደሚዘልቅ በተደጋጋሚ ቃል እየገቡ ነው።

በተለያዩ መንገዶች ከኀብረተሰቡ ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን በቅርቡ ከግድቡ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በተመሳሳይ መልኩ በዱባይ እና በሰሜን ኢምሬትስ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት ድጋፋቸውን አጠናክረው በመቀጠል የቦንድ ግዥ አከናውነዋል።

በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንፅላ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ይበልጣል አእምሮ እንደገለጹት፤ የግድቡ መሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድርግ በዱባይና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን 152 ሺ ዶላር የቦንድ ግዢ ፈጽመዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት እስካሁን በዱባይና በአካባቢው ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር የቦንድ ግዢ ማድረጋቸው ነው ያመለከቱት።

በዱባይ ነዋሪ የሆኑት የአል ሀበሻ ሬስቶራንት ባለቤት ወይዘሮ ሳራ አራዲ በቤተሰቦቻቸውና በድርጅታቸው ስም የ250ሺ የአሜሪካ ዶላር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያውሉትን ድጋፍ አጠናክረው ለመቀጠል መወሰናቸውን ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ ከ57 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፤ የግድቡ አርማታ ሙሌት ሥራም 72 በመቶ ያህል መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተደረገለት የማሻሻያ ሥራዎች ኃይል የማመንጨት አቅሙ ወደ 6 ሺ450 ሜጋ ዋት ከፍ ማለቱ ይታውቃል።

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2009/ኢዜአ/